ቀጥታ፡

ስምምነቱ በእውቀት ሽግግርና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012(ኢዜአ) የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

ዛሬ የተካሄደው ስምምነት የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን በስፋት መጠቀም የሚያስችል ነው ተብሏል።

ስምምነቱን የፈረሙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም በዚህ ወቅት እንደገለጹት አገሪቱ ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ ለመጠቀም ተቋማት በጋራ መስራት ያለባቸውን ለይቶ ከማከናወን አኳያ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

በተለይ ትኩረት የሚሰጥባቸውና አገሪቱን ወደ ላቀ ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉ ዘርፎችን ለይቶ በስፋት እንዲሰራባቸው በማድረግ በኩል ክፍተቶች አሉ።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማዕድን ዘርፍ ያለውን እምቅ ሃብት ለመጠቀም ብሎም በጋራ ለመስራት ከማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ጋር በዛሬው ዕለት የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም ገልጸዋል።  

ስምምነቱ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ላይ በስፋት መስራት የሚያስችልና ብቁ ሙያተኞችን ወደ ዘርፉ በማስገባት የአገሪቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ማሳደግን ዓላማው ያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል።

በተለይም በዘርፉ የተሰማሩ ነባር ሙያተኞች ምርምር የሚያደርጉበትን ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር በእውቀት ሽግግር ላይም የሚኖረው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የገለጹት።

 ስምምነቱ በመደበኛው የከፍተኛ ትምህርት ላይ ላሉ የዘርፉ ተማሪዎች አጫጭር ስልጠናዎችን በጋራ መስጠትና ምርምር ማካሄድን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም ዘርፉ የሚፈልገውን ተጨባጭ ፍላጎት በመለየት ከአገር ውስጥና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር በጋራ የሚሰራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያስችላል።

በቴክኒክና ሙያ ዘርፍም እንዲሁ ሙያተኞችን በማብቃት እውቀታቸውን በተግባር እንዲሞክሩ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር በስምምነቱ መካተቱንን ሚኒስትሯ አከለዋል።

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ኡርቀቶ በበኩላቸው የማዕድን ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እየተሰራበት ባለመሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ አድርጓታል።

ይህን ለመለወጥ የተማረ የሰው ኃይል በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገባ ማድረግና የሌሎች ስኬታማ አገራትን ልምድ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ዶክተር ሳሙኤል እንዳሉት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ዛሬ የተደረገው ስምምነት በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን ለማግኘት ከማገዝ ባለፈ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።

በተለይም ዘርፉን ለማሳደግ የተሻለ እውቀትና የሥራ ተነሳሽነት ያላቸውን ሙያተኞች በስፋት በማሰማራት በኩል ስምምነቱ ጠቃሚ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

የሥራ ዕድል በመፍጠርና በውጭ ምንዛሬ ተገዝተው የሚገቡትን በአገር ውስጥ ለመተካትና አገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ስምምነቱ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በተደረገው ስምምነት መሰረት ውጤታማ ሥራዎችን ለማከናወን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

ስምምነቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም