ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች ከቫይረሱ አጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) ድንበር ተሻግረው ወደ ድሬዳዋ የሚገቡና ሚወጡ ተሽከርካሪዎች ከኮሮና ቫይረስ አጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ገለጹ።

በግብረ ኃይሉ የጤናው ዘርፍ አስተባባሪና የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ለኢዜአ  እንደተናገሩት ዕቃ ጭነው ከጅቡቲ ወደ ድሬዳዋ የሚገቡና የሚወጡ አሽከርካሪዎች ለጥንቃቄ የሙቀት ልኬት እየተደረገላቸው ነው።

ወደ ከተማ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች  ፀረ-ተዋህስያን እንደሚረጩም አመልክተዋል።

"አስፈላጊው የመከላከያ ትምህርት ይሰጣል፤ ጭንብልና ጓንት እንዲጠቀሙና የመከላከያ ዘዴዎች እንዲተገብሩ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል፡፡

ለጥንቃቄም ከጅቡቲ የሚመጡ አሽከርካሪዎችና  ተሽከርካሪዎች  አንድ ቦታ ላይ ማሳደር እንደሚጀመርና የማስተማሩ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ወይዘሮ ለምለም አስታውቀዋል፡፡

አሽከርካሪዎች ለሀገሪቱ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት ዕድገት መሰረት በሆነው ታላቅ ተግባር በተሰማሩበት ሁኔታ  ለአፍታ ቢሆን ሳይዘናጉ ከቫይረሱ ራሳቸውን የመጠበቅ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡


በግብረ ኃይሉ የጸጥታው ዘርፍ አስተባባሪና የአስተዳደር ፖሊስ  ኮሚሽነር አለሙ ሙግራ በበኩላቸው " በድንበር አካባቢ የሚደረገው የተቀናጀ ክትትልና ድጋፍ የሀገርና የዜጎችን የጋራ ጤንነት የመጠበቅ ጉዳይ ነው" ብለዋል፡፡

የጅቡቲ ተመላሾችን የህብረተሰብን አደረጃጀት በመጠቀም  ለጥንቃቄ  ወደ ጤና ተቋማት መጥተው ምርመራ እንዲያደርጉ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ከከባድ መኪና አሽከርካሪዎች መካከል  አቶ ካሊድ አብዱልቃድር ለኢዜአ እንደገለጹት በጅቡቲ እየጨመረ ከሚገኘው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አንጻር የሚደረገው ክትትል ጥሩ ቢሆንም ከልክ ያለፈው  ቁጥጥሩ በህብረተሰቡ ዘንድ መገለል እያስከተለ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል፡፡

ሌላው አሸከርካሪ ጅብሪል ኡስማኤል በበኩላቸው "ህብረተሰቡ እንደቤተሰቡ እንዲመለከተን እንፈልጋለን፤ ባገኘነው ትምህርት ራሳችንና ቤተሰባችን ለመጠበቅ ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን" ብለዋል ፡፡

በድንበር ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ጥሩ ቢሆንም ለፀረ- ተዋህስያን ተብሎ የሚረጨው ኬሚካል ህጋዊነት በሌላቸው ሰዎች ገንዘብ እየተጠየቁ  በመሆኑ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ አቶ ፀጋዬ አርአያ ናቸው፡፡

ከባድ ተሽከርካሪዎች በሚሰበሰቡበት አካባቢ በምግብ ዝግጅት የተሰማራችው ወጣት መሰረት ጌታቸው በበኩሏ የሾፌሮቹ መኖር ለአካባቢው ህብረተሰብ የገቢ  ምንጭ መሆናቸውን ገልፃለች፡፡

የሚተላለፉ የኮሮና መከላከያ መመሪያዎችን በማክበርና ከንክኪ በመራቅ ስራቸውን በጥንቃቄ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም