ህጻናት የእናት ጡት ወተትን ያለማቋረጥ እንዲያገኙ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 ለህፃናት የወደፊት ዘላቂ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት የእናት ጡት ከምንም ነገር በላይ ወሳኝ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ። በመሆኑም ማንኛውም ጨቅላ ህፃን ስድስት ወር እስኪሞላው ድረስ ከእናቱ የጡት ወተት ውጭ ሌላ ነገር እንዲመገብ አይመከርም። እንዲያም ሆኖ ግን በአገሪቱ በተለያየ ተቋም የሚሰሩ እናቶች ከጨቅላ ልጆቻቸው ጋር ሆነው ይህንን ተግባር በብቃት መተግበር አይችሉም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በአገሪቱ ህግ መሰረት ለወላድ እናት የሚሰጠው የእረፍት ጊዜ ስድስት ወር የማይሞላ በመሆኑ ነው። የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሰራተኛ እናቶች ከወሊደ በኋላ ለጨቅላ ህጻናት ልጆቻቸው የጡት ወተትን ያለማቋረጥ የሚሰጡበትን ሁኔታ የሚያመቻች የሙከራ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል። በፕሮጀክቱ መሰረት እናቶች የጡታቸውን ወተት በጥንቃቄ አልበው ለልጆቻቸው እንዲመግቡ ይደረጋል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የህብረተሰብ ጤና ክፍል ውስጥ የእናቶች ስነ-ተዋልዶ ጤና መምህር እና የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ ዶክተር እውነት ገብረሃና  እንደሚሉት፤ ፕሮጀክቱ ከወሊድ በኋላ ወደ ስራ የሚመለሱ እናቶች ለልጆቻቸው የሚሰጡትን የጡት ወተት ሳያቋርጡ እንዲቀጥሉ የሚያበረታታ ነው። እናቶች በስራ ምክንያት ከልጆቻቸው ጋር በማይውሉበት ጊዜ የጡት ወተት እንዳያጡ ለማድረግ በስራ ቦታ በሚዘጋጅላቸው ክፍል የጡታቸውን ወተት አልበው እንዲያስቀምጡ እንደሚደረግ ገልጸዋል። ማንነታቸውን በግልፅ በሚጠቁም መልኩም የሚታለበው የጡት ወተት በማቀዝቀዣ ውስጥ ይቆያል፤ ከሥራ በኋላም የታለበውን ወተት ወደየቤታቸው ይዘው በመሄድ እስከተከታዩ ቀን ማቀዝቀዣ ውስጥ ያስቀምጣሉ። እናቶቹ ታዲያ በተከታዩ ቀን ወደ ስራ በሚሄዱበት ወቅት ህፃናቱን የሚንከባከቡ አካላት ታልቦ ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠውን ወተት ለህፃናቱ ይመግባሉ። ወተቱ ከታለበ በኋላም በባክቴሪያ እንዳይጠቃ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚደረግ መሆኑንም ዶክተር እውነት ገልጸዋል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናቶች ዳይሬክቶሬት የስርዓተ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ሂወት ዳርሰኔ  እንደሚሉት፤ እናቶች ስድስት ወር ላልሞላቸው ጨቅላ ልጆቻቸው የላም ሆነ ሌላ ወተት እንዳይሰጡ ፕሮጀክቱ ያበረታታቸዋል። ፕሮጀክቱ የህጻናት ዘላቂ ጤና ለማስጠበቅ ከማገዝ ባሻገር እናቶችን ከጡት ካንሰር ለመከላከል የሚያግዘ መሆኑም ተጠቁሟል። እናቶች ለልጆቻቸው የጡት ወተት መመገብን ቢያዘወትሩ ለሌሎች ተኪ ምግቦች የሚያወጡትን ወጪ ሙሉ በሙሉ መቀነስ እንደሚያስችላቸው ተገልጿል። ፕሮጀክቱ በሚቀጥለው ወር ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን የመጀመሪያው ሙከራ የሚተገበረው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኙ እናቶች ላይ ነው። በቀጣይም ግንዛቤ በመፍጠር በሁሉም የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ መያዙ ተነግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም