የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስፔን አቻቸው አራንቻ ጎንዛሊዝ ጋር በስልክ ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስፔን አቻቸው አራንቻ ጎንዛሊዝ ጋር በስልክ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012(ኢዜአ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስፔን አቻቸው አራንቻ ጎንዛሊዝ ጋር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በትብብር ለመከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በስልክ ተወያዩ።
የሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የትብብር ግንኙነቶችን ማጠናከር በሚቻልባቸው እንዲሁም የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን በጋራ ለመከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።
የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ስፔን በሁለትዮሽ እና በአውሮፓ ህብረት በኩል ለኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ድጋፍ በተመለከተ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዓለም እየጠፋ ባለው የሰው ህይወት የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ያለውን ጥረት በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እስከዛሬ ድረስ ያደረጓቸውን ውይይቶች በተመለከተም ተናግረዋል።
የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራንቻ ጎንዛሊዝ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ስለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነዋል።
ስፔን ከኢትየጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ግንኘነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ከመሆኑም ባሻገር ስለበሽታው ያልታወቁ በርካታ ጉዳዮች ስላሉ የሁሉም አካላት ትብብር በእጅጉ ወሳኝ ነውም ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚገነዘቡና ሶስቱ አገሮች ልዮነታቸውን በውይይት መፍታት እንዳለበቸውም ገልጸዋል።
የናይል ወንዝ ቀጠናዊ ትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያመጣ መልኩ ተመስርቶ መንቀሳቀስ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸዋል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያደረሰን መረጃ ያመለክታል።