ቀጥታ፡

ከሳዑዲ አረቢያና ኩዌት ከ1 ሺህ 484 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው ይገባሉ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012 (ኢዜአ) በተያዘውና በቀጣዩ ሳምንት ከሳዑዲ አረቢያና ከኩዌት ከ1 ሺህ 484 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ጋር በተያያዘም በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ይነገራል።

በዚህም ዜጎቹን ወደ አገራቸው ለመመለስ የኢትዮጵያ መንግስት እየሰራ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንጽላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተስፋኪሮስ ኃይሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያኑን ስደተኞች በውጭ ጉዳይ፣ በሠራተኛና ማህበራዊ እንዲሁም በሰላም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ትብብር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በዚህ ሳምንትም በሳዑዲ አረቢያና በኩዌት የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ከአገራቱ መንግስታት ጋር በመነጋገር ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ተስፋኪሮስ እንዳሉት በተያዘው ሳምንት በሳዑዲ አረቢያ "ዲዛን" በተበለ እስር ቤት የነበሩ 473 ዜጎች ወደ አገራቸው ይመጣሉ።

ከነዚህ በተጨማሪ በቀጣዩ ሳምንት 1 ሺህ 11 ዜጎች ከኩዌት ወደአገራቸው እንደሚገቡ አመልክተዋል።

እነዚህ ዜጎች በእስር ቤትና በመጠለያ ውስጥ የነበሩና ይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸውን የተናገሩት ዳይሬክተር ጀኔራሉ፣  የስደት ተመላሹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

መንግስት እንደነዚህ ላሉ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ወደ አገራቸው እንዲመሉ የማድርግ ሥራውን እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በሊባኖስ ቤይሩት ይኖሩ የነበሩ 656 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በመንግስት ሙሉ ወጪ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም