ወረርሺኙን ለመከላከል አግባብነት ያለው ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ሙህራን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
ወረርሺኙን ለመከላከል አግባብነት ያለው ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ሙህራን ተናገሩ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24/2012( ኢዜአ) በኮቪድ- 19ና በመሳሰሉ ወረርሺኝ ወቅት የኅብረተሰቡን ሥነ ልቦና ጫና ውስጥ በመክተት አዳዲስ ባህሪያት እንዲይዙ የሚያደርጉ ክስተቶች እንደሚፈጠሩ ሙህራን ተናገሩ።
አዲስ ወግ ዌብ ነር -2- "ፈጠራ በቀውስ ጊዜ" በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሙህራን እንደገለጹት፤ እንደ ኮቪድ19 ያሉ ተላላፊ በሽታዎች በዓለም ላይ በተደጋጋሚ ተከስተዋል።
እነዚህም ወረርሺኞች ኅብረተሰቡ ላይ አሉታዊም ሆነ አውንታዊ ጫና ፈጥረው እንደሚያልፉም ሙህራኑ አስረድተዋል።
በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፣ ወረርሺኝ በሀገሪቱ ላይ በሚከሰትበት ጊዜ ኅብረተሰቡ ወረርሺኙን ከፈጣሪ በሰው ልጅ ኃጥያአት ምክንያት የመጣ ቁጣ አድርገው በመውሰድ በስነ ልቦናቸው ውስጥ ጫና እንደሚያሳድሩ ያስታውሳሉ።
ጫናውም ኅብረተሰቡ በፍርሃት እንዲዋጥና ወረርሽኙንም በኃጥያአት ምክንያት አመጡት የሚሏቸውን ሰዎች አስከማግለል እንደሚደርሱ አስረድተዋል።
የአይምሮ ሀኪሙ ዶክተር ቢኒያም ወርቁ በበኩላቸው፤ ወረርሺኞች አውንታዊም ሆነ አሉታዊ ጎኖች አላቸው ይላሉ።
ከአውንታዊ ነገሮች ሲነሱ ሰዎች ራሳቸውን በተገቢው መልኩ ከወረርሽኙ እንዲጠበቁ አካላዊ ንጽህናቸውን መጠበቅና ከበሽተኛው ሰው ራሳቸውን በማራቅ፣ በመራቅና ርቀትን በመጠበቅ የመከላከል ሥራዎችን በአግባቡ በማከናወን የዕየለት ሥራቸው ያደርጉታል በማለት ያስረዳሉ።
አሉታዊ ጎኑንም ባነሱበት መልዕክታቸው፤ኅብረተሰቡ ከልክ ያለፈ ፍርሃት በራሱ ላይ መፍጠርና በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች ላይ አድሎና መገለል በመፍጠር የሥነ ልቦና ጫና ማሳደር ነው ይላሉ።
በዚህ ጊዜ ሰውን ከበሽታ የሚከላከሉ ሁለት ነገሮች አሉ ይላሉ ዶክተር ቢኒያም፤ አንደኛው የመከላከለ አካላዊ አቅም ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የመከላከል አቅም ደግሞ ባህሪያዊ ነው።
አካላዊ የሚባለው ሰውነታችን በሽታን የመከላከል አቅሙን የሚያሳድግበት ዘዴ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሽታው የሚጠይቀውን የሥነ ልቦና ዝግጅትና የባህሪ ለውጥ ማምጣት ነው በማለት ያስረዳሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ አካላዊ የመከላከል አቅምን ለመፍጠር አስቸጋሪ ሁኔታን እያመጣ ስለሆነ የባህሪ ለውጥ ማምጣት ግድ ነው ይላሉ ዶክተር ብንያም።
በመሆኑም አሁን በሽታውን ለመከላከል እየተጠቀምንበት ያለውን እጅን በሳሙናና ውሃ ቶሎ ቶሎ የመታጠብ፣ አካላዊ ርቀትን የመጠበቅና አፍና አፍንጫን የመሸፈን ተግባርን የመላበሰ ባህሪን በማጎልበት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል በማለት ይመክራሉ ዶክተር ቢኒያም ወርቁ።
በወረርሺኝ ጊዜ በአይምሮአችን ሦስት ነገሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ የሚሉት ደግሞ የስነ ልቦና ባለሙያዋ ዶክተር ባርኮት ሚልኪያስ ናቸው።
ዶክተር ባርኮት እንደሚናገሩት፤ በእንደዚህ ዓይነት ወረርሺኝ ወቅት አይምሮአችን የተጋነነና ከልክ ያለፈ ጥንቃቄ ያለው ምላሽ፣ አግባብ ያለው ምላሽና የተገደበ ምላሽ ይሰጣል።
ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ የተጋነነ ምላሽም ሆነ የተገደበ ምላሽ ለሁኔታው መስጠት የሥነ ልቦና ጫና ይፈጥራሉ ይላሉ ባለሙያዋ።
በመሆኑም ለዚህ ዓይነቱ ሥጋት ዓይምሮአችን ሁኔታውን ያገናዘበ አግባብ ያለው ማለትም በሀኪሞችና በዘርፉ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክሮች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ነው ይላሉ።