ከወረርሽኙ በተጓዳኝ ምርታማነትን ለማሳደግ መረባረብ ይገባል

105

ሐዋሳ፣ ግንቦት 23/2012 (ኢዜአ) በሃገሪቱ የኮሮና ወረርሽኝን ከመከላከሉ ጎን ለጎን በዘንድሮው የመኸር አዝመራ ምርታማነትን ለማሳደግ መረባረብ እንደሚገባ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት አሳሰበ።


የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በደቡብ ክልል ስልጤና ጉራጌ ዞኖች እየተካሄደ ያለውን  የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ትናንት ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ ብናልፍ አንዱአለም  እንደገለፁት ወረርሽኙ በሃገሪቱ እየተስፋፋ በመምጣቱ በጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ሊያሳርፍ ይችላል።

በመሆኑም ወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያስከትልና ኢኮኖሚያችን እንዳይጎዳ ምርታማነትን ለማሳደግ አቀናጅቶ መስራትና መረባረብን ይጠይቃል ብለዋል።

በዚህ ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በመቃኘት የህብረተሰቡንና የአመራሩ ትስስር ያለበትን ሁኔታ ለማየት አላማ ያደረገ ጉብኝት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በየደረጃው የሚገኘው አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጽህፈት ቤቱ ለማብቃትና ለመደገፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል ።

ከግብርና ስራ ጋር በማያያዝ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ ልማትን ለማሳካት በችግኝ ጣቢያዎች እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እጅግ የሚያበረታቱ ናቸው ብለዋል ።

የምናለማቸው ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚያስገኙ መሆን አለባቸው ያሉት ኃላፊው፤ በዚህ ረገድ በደቡብ ክልል ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አድንቀዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ በበኩላቸው ወረርሽኙ በኢኮኖሚ፣ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ዘርፎች ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በወረርሽኙ ሳቢያ በዓለም ላይ የኢኮኖሚ ውድቀት ሊደርስ ይችላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፤ በሀገራችንም መሰል ተፅዕኖ እንዳያጋጥም መንግስት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በጉብኝቱ ወቅት በጉራጌ ዞን የቡታጅራ ችግኝ ማባዣ ማዕከል ኃላፊ አቶ አመርጋ መንጂ እንዳብራሩት ማዕከሉ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር  በ2010 የተቋቋመው በኢትዮጵያና  በእስራኤል መንግስታትና  በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ትብብር መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነት የእስራኤል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የአቮካዶ ችግኞች  በማባዛት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ ሲሆን እስከ አሁን የኤክስፖርት ምርት ዝርያ የሆነ ከ208 ሺህ በላይ ችግኞች በማዘጋጀት ለተለያዩ ክልሎች ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ በራሱ ገቢ ለመተዳደር አቅም መፍጠሩን ያመለከቱት አቶ አመርጋ ባለፈው ዓመት ብቻ ከምርት ሽያጭ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን  ብር ገቢ አግኝቷል ።

በስልጤ ዞን መስቃን ወረዳ የአቮካዶ አምራች አርሶ አደር ኑሪ አወል በበኩላቸው ባላቸው ሁለት ሄክታር መሬት ላይ 1 ሺህ 150 የአቮካዶ ችግኝ በማልማት ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ልማቱን ለማስፋፋት ፍላጎት ቢኖራቸውም በውሃ እጥረት ምክንያት መስተጓጎሉን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ብቻ ከምርት ሽያጭ 90 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ገልፀዋል ።

የደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ዳምጠው እንዳሉት ደግሞ በክልሉ በ1 ሺህ 500 ክላስተሮች የፍራፍሬ ልማት እየተካሄደ ነው ።

በአጠቃላይ ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ገበያ ተኮር በሆኑ የፍራፍሬ ልማቶች ላይ በመሰማራት አርሶ አደሩ ህይወቱን መቀየር እንደቻለ አብራርተዋል።    

የከፍተኛ አመራሮቹ የኩታ ገጠም አርሻ ልማት ፣ የችግኝ ተከላ ምርጥ ተሞክሮና በኮሮና ቫይረስ መከላከል ዙርያ እየተከናወኑ ያሉት ስራዎችን ተመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም