ቀጥታ፡

ለጋራ ጥቅም በጋራ መስራት

በሰውነት ጀምበሩ (ኢዜአ)

ለሰው ልጆች ህይወት አስፈላጊ ከሆኑት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት ውሃ  አንዱ ነው። ይህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ውሃ በአግባቡ ካልተያዘ ጎሮቤት ከጎሮቤት፤መንደር ከመንደር፤ ወረዳ ከወረዳ፤ ክልል ከክልል ጋር ሊያጋጭና ሊያቃቅር ይችላል። ከዚህም ሲያልፍ ድንበር ዘለል ወንዞች በሀገራት መካከል ጥልና ከዚያም አልፎ ጦርነት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ።

ጥቁር አባይ ከኢትዮጵያ ደጋማዎቹ ስፍራዎች የሚመነጭ ሲሆን፤ ከነጭ አባይ ጋር ተቀላቅለው በሱዳን ርዕስ ከተማ ካርቱም አድርጎ  ወደ ግብፅ  ለዘመናት ፈሰዋል። አባይ ወይም ናይል በዓለም ረዥሙ ወንዝ ና አሥራ አንድ አገሮችን አቆራርጦ የሚያልፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ነው።

ወደ ታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ወደ ሱዳንና ግብፅ  85 በመቶ የሚሆነው የውሃ ፍሰት    የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ጥቁር አባይ ሲሆን፤ ቀሪው 15 በመቶ የሚሆነውን  ደግሞ ነጭ አባይ ተብሎ ከሚጠራው ወንዝ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በዚሁ ወንዝ ላይ የሚገነባው ታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅም በሃገሪቱ ያለውን የሃይል እጥረት የሚቀርፍ ከመሆኑ ባሻገር፤ ለጎረቤት ሃገሮች ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ግድብ እውን ሲሆን ለኢትዮጵያ ከሚሰጠው ጥቅም ባልተናነሰ መልኩ ለታችኞች ተፋሰስ አገራት አያሌ ጥቅሞችን ይሰጣል። ይህ በሦስቱ የተፋሰስ ሃገሮች የሚኖረው ዝምድናና መቀራረብን ያጠናክራል ተብሎ ይታሰባል።

ከዚህ በተጨማሪ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የህዳሴው ግድብ ለዜጎች ብዙ የሥራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር፤ የአሣ ሃብት ልማትም የሚካሄድበት ነው። ግድቡ ለሃይል ማመንጫ እንጂ ለመስኖና ለደን ልማት ስላልሆነ በግብፅና በሱዳን ላይ የሚያሳድረው ስጋት አይኖርም።

የኢፌዲሪ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚያመለክተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታው ሲጠናቀቅ ለኢትዮዽያ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች በብዙ እጥፍ ለታችኞች ተፋሰስ አገራት ማለትም ለግብጽና ለሱዳን  ይሰጣል።

ከጥቅሞቹም መካከል በሱዳን የሚገኙ ሮዞረስ ሰናርና ሜሮው የሀይል ማመንጫ ግድቦች ሀይል የማመንጫት አቅማቸውን በዕጥፍ እንደሚያሳድግላቸው ሰነዱ ያብራራል።  እነዚህ ግድቦች ተጠቃሚ የሚሆኑት በደረቃማ ወቅትም የተመጠነ እና መደበኛ ፍሰቱን የጠበቀ ውሃ እንዲኖር ያደርጋል። በዚህም ከፍተኛ የውሃ ሀይል ሲጨምር የማመንጨት አቅማቸውም በዚያው ልክ ያሳድግላቸዋል።

በሌላ በኩል በየጊዜው ሂደቱን ጠብቆ የሚፈሰው የውሃ መጠን የውሃ ማመንጫ ተርባይኖችን በሚገባ እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ከመጠን በላይ በሆነ ጎርፍና ናዳ ከአገልግሎት ውጭ እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል።

ሌላው ግድቡ ለታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ከሚሰጠው ጥቅም መካከል ውሃ የመያዝንና የማጠራቀምን አቅም በማዳበር በቀጠናው ያለውን የውሃ መሰረተ ልማት በማሳደግ የዕድገት መጠኑን ወደ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያሳድገዋል ይላል መረጃው። ይህም ከዚህ በፊት 59 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የነበረውን በማሻሻል ሊሰጥ የሚችለውን ጥቅም ያሳድገዋል።

በዚህም የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲወኖር በማድረግ የተቆራረጠ የውሃ ፍሰትን ይከላከልል። ይህ አሰራርም ውሃን በመቆጠብ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ከድርቅና ከአላስፈላጊ ጎርፍ እንዲድኑ ያደርጋ ነው የተባለው።

በተጨማሪም በሰነዱ ላይ እንደሰፈረው ግድቡ ሲጠናቀቅ ውሃው በተመጠነ መልኩ እንዲፈስ በማድረግ ለመስኖ ልማት ያግዛል፣  ለቱሪዝም ፍሰትም ጉልህ ሚና ይጫወታል። 

በሌላ በኩል የታችኞቹን የተፋሰስ አገራት የግድቦችን አቅም በማጎልበት አላስፈላጊ ወጭንና  ጭንቀትን በመቀነስ የውሃ ስርገትን ከመከላከል በተጨማሪም በየዓመቱ በሱዳን የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ እና በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግድቦች የሚከማቸው ደለል እንዲቀንስ ያግዛል ሲልም ሰነዱ ያብራራል።

ሌላው የግድቡ እውን መሆን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ውሃ መጠራቀም መቻሉ በውሃ ትነት በአመት ከ6 እስከ 16 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ይቀንስ የነበረውን በአማካኝ ወደ 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ዝቅ እንደሚያደርገው ተገልጿል።

ይህ የህዳሴ ግድብ ውሃ የመያዝ አቅም በማዳበር በከፍታ ቦታ ውሃን የማቆር ስራ በማዳበር ሊባክን የሚችለውን ውሃ ከመቆጠቡም በላይ የውሃውን የፍሰት ሚዛን ይጠብቀዋል። ይህም በበረሃ አካባቢ ሊባክን የሚችለውን ከ10 እስከ 15 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደሚያስቀር በሰነዱ ተብራርቷል።

እንደ ሰነዱ ከሆነ ግድቡ እውን ሲሆን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በተከታታይ ከ1988 እስከ 2002 በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት የሚያደርሰውን የጎርፍ ጫና በማስቀረት የነበረባቸውን አገራዊ ስጋት ያስቀራል። እኤአ በ2007 ዓባይ በገፍ ሞልቶ ጎርፍ በሱዳን ለብዙዎቹ ህይወት መቀጠፍና ሀብት ንብረት አውድሟል። እናም ይህ ግድብ ለኢትዮጵያ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በዘለለ ለእነዚህ አገራት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል።

በዋናነት ይህ ግድብ ሊሰጣቸው ከሚችላቸው ጥቅሞች በበለጠ ከዚህ በፊት አባይ የኢትዮጵያን ከፍተኛ ቦታዎች በጎርፍ ተጠርጎ በሚሄዱ ደለሎችና አሸዋ የአስዋን ግድብ ህልውና ብቻም ሳይሆን በሱዳን የሚገኙ ግድቦችን ሲፈታተን የቆየ ሀቅ ነው። በመሆኑም አሁን እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 50 በመቶ የደለሉን መጠን በመቀነስ የግድቦችን ህልውና እንደሚያሳድገው ሰነዱ ያብራራል።  ይህ የተጨማሪ ግድብ ፍላጎትን በማስቀረት ሊያወጡት የነበረውን አገራዊ ወጪ ይቆጥብላቸዋል።

በተጨማሪም የታችኞች ተፋሰስ አገራት በድርቅ ጊዜ የሚያጋጥማቸውን አስከፊ ክስተት በመቀነስ በተለይ በሱዳን እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር ከ1980 እስከ 85  አጋጥሞ የነበረውን የመስኖ እርሻ መቀነስ አደጋ  በመፍታትና የግብጽን የውሃ ባንክ ይዞታ እንደሚያሳድግላት በሰነዱ ተገልጿል።

በጥቅሉ ከግድቡ የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ በመጠቀም በቀጣናው ያለውን የኃይል እጥረትና ብክነት ለመቋቋም እንደሚያስችል ያመላከተው ሰነዱ፤ በዚህም ሱዳንና ግብፅ ዋነኛ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። ግድቡ የውኃ ኃይል ማመንጫ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ነፃ በመሆኑ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢ ሥነ ምኅዳርንም በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም በባለሙያዎች ተገምግሟል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የሚያጡትን ገቢ ያስቀራልም ተብሏል።

ግብጻዊያን ወደ 55 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መጠን ያለው የከርሰ ምድር ውኃ ክምችት እንዳላቸውና ይህም ከኢትዮጵያ ጋር ሲነጻጸር የአምስት ዕጥፍ ብልጫ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። በመሆኑም ጥቅሙ ለሁሉም የሆነን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታን ተባብሮ በማጠናቀቅ  ከጥቅሙ ተቋዳሽ ለመሆን በጋራ መስራት ይገባል መልዕክታችን ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም