ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ አገኘ
ነቀምቴ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለለይቶ ማቆያ አገልግሎት የሚውል ከ500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ።
ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ያገኘው ከዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ነው።
የማኅበሩ ተወካይ አቶ ፍሬው ኃይሉ ድጋፉን ለዩኒቨርሲቲው ባስረከቡበት ወቅት ፍራሽ፣ አንሶላ፣ ብርድ ልብስና የተለያዩ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ በመጠበቅ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ መፍጠሪያ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን አቶ ፍሬው ተናግረዋል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የለይቶ ማቆያ አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት በማሟላት ቀደም ብለው ማዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል።
የዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማኅበር ለለይቶ ማቆያው አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን በድጋፍ ለዩኒቨርሲቲው ማበርከቱ ሥራውን ለማጠናከር እንደሚያግዝ በመግለጽ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የምሥራቅ ወለጋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ሲስተር መሰለች ረጋሣ ለዩኒቨርሲቲው የተደረገው ድጋፍ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።