አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ለኮሮና መከላከል አንድ ሚሊዮን የሚገመት ድጋፍ አደረገ

67

አሶሳ፣ ግንቦት 22 /2012 (ኢዜአ) አሶሳ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ምግብና የተለያዩ ግብአቶችን ለቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ዛሬ አስረከበ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የኮሮና መከላከል ግብረኃይል ሰብሳቢ አቶ አሻድሊ ሐሰን ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ እንደተናሩት በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረግው ጥረት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊታገዝ ይገባል።

ይህም የበሽታውን ሥርጭት በማቆም የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ወሳኝ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"ቫይረሱን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተደርጓል፤ በተለይም የድንበር አካባቢ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

ሁሉም ሰው ከቤት ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያደርግ የተቀመጠውን ድንጋጌ ለማስተግበር በጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት የተደራጁ "ማስክ" አምርተው እንዲያቀርቡ ጥረት መጀመሩን አመልክተዋል።

"በተለይም ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰቡባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደንበኞቻቸው ማክስ ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።

አሶሳ ከተማ  የግብይት ማዕከላትን የማብዛት ሥራ በሌሎች የክልሉ ከተሞች ተግባራዊ እንዲደረግ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያደረገው ድጋፍ በክልሉ የመከላከል ሥራውን እንደሚያጠናከር ገልጸው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው ለቫይረሱ መከላከል ዛሬ ያስረከባቸው ድጋፎች  አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ገልጸዋል።

ለግብረ ኃይሉ የባረከቱት ድጋፍ ከቀረቡት መካከል ጤፍ፣ ሩዝ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ጨው እና ሌሎችም ግብአቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም