በኮቪድ-19 ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎችን የሚለይ "ደቦ" የተሰኘ ሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኮቪድ-19 ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎችን የሚለይ "ደቦ" የተሰኘ ሞባይል መተግበሪያ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኮቪድ-19 ከተያዘ ሰው ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው ሰዎችን የሚለይ "ደቦ" የተሰኘ የአንድሮይድ ሞባይል መተግበሪያ ይፋ አደረገ።
ማንኛውም የአንድሮይድ ሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ግለሰብ በየትኛውም ቦታና ጊዜ የስልኩን ብሉቱዝ በመክፈት ብቻ መጠቀም ይችላል ተብሏል።
ኢንስቲትዩቱ ከ''ደቦ'' በተጨማሪ ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ /Covid-19 Ethiopia/ የተባለ የሕክምና ባለሙያዎች ዕውቀት የሚያገኙበት መተግበሪያን በተመለከተም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ዓባይነህ እንዳሉት ''ደቦ'' የአንድሮይድ ስልክ መተግበሪያ ከሰዎች የተደበቁ ግለሰቦችን ለመለየት ያስችላል።
በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች መልካም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፡ የማስታወስ ችሎታቸውን በማጣት፤ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚ ያገኟቸውን ባለመለየታቸው የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎችን መለየት አስቸጋሪ እንዳደረገው አስረድተዋል።
በመሆኑም ከሁለት ሜትር ርቀት በታች ከ14 ቀን በፊት በትራንስፖርት፣ በገበያ፣ በገንዘብ ልውውጥ፣ በአምልኮ ቦታ ወይም በሌሎች መንገዶች ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች በሙሉ የሚያሳይ መተግበሪያ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።
መተግበሪያው በአንድሮይድ ስልኮች ብሉቱዝ በማብራት ብቻ መጠቀም እንደሚቻል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
መተግበሪያውን ለመጠቀም በቅድሚያ ክልል፣ ወረዳ፣ ሥምና ስልክ ቁጥር መሙላት እንደሚገባ አመልክተው፤ መተግበሪያው እንደተጫነ ብሉቱዙ በራሱ ይበራል ብለዋል።
በማንኛውም ቦታ ሲንቀሳቀሱ ከሁለት ሜትር ርቀት በታች የሆኑ የመተግበሪያው ተጠቃሚ ሰዎችን የብሉቱዝ ኮድ በምስጢር እንዲለዋወጡ ያደርጋል።
መተግበሪያውን ከሚጠቀሙ ሰዎች አንዱ በቫይረሱ ተይዞ ከተገኘ ንክኪ የሚለየው የጤና ቡድን የምስጢር ቁጥሩን በማስገባት ከግለሰቦች ጋር የነበረውን ግንኙነት በዝርዝር እንደሚያሳይ አቶ አስቻለው አስረድተዋል።
መተግበሪያው ከሰዎች ሥም፣ አድራሻና ስልክ ቁጥር ውጭ ያሉ ግለ ታሪኮችን እንደማያሳይም ገልጸዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ የአንድሮይድ ሞባይል መተግበሪያ ስልኮችን በመጠቀም የበሽታውን ሥርጭት መግታትና ወገኑን እንዲያድን ጠይቀዋል።
መተግበሪያውን በ debo.ephi.gov.et የሚለውን ድረ ገጽ በመጎብኘት ማግኘት ይቻላል ተብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የኮቪድ-19 ሕክምና የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ተመሳሳይ ግንዛቤና ዕውቀት የሚሰጥ የሞባይል መተግበሪያ ይፋ ተደርጓል።
ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ (Covid-19 Ethiopia) የተባለው መተግበሪያ ባለሙያዎቹ ባሉበት ቦታ ሆነው ከቫይረሱ ጋር የተያያዘ መረጃ የሚያገኙበት ነው።
የበሽታ ቅኝትና አሰሳ፣ የሕሙማን አያያዝ፣ የላቦራቶሪ አገልግሎት፣ ብክለትን መከላከልና መቆጣጠር የአደጋ ሥጋት ተግባቦትና የኅብረተሰብ ተሳትፎ እንዲሁም የኮቪድ-19 መሠረታዊ የጤና ክብካቤ መመሪያዎችን ማግኘት እንደሚያስችል ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።