ቀጥታ፡

አዋጁን ተላልፈው ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ ሰዎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል---የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22/2012  (ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመተላለፍ ሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ ሰዎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግሥት የሕግ የባላይነትን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሰራም ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ መንግሥት ዜጎችን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ ጥረት እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሕዝቡን ለሰላማዊ ሰልፍ የሚጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ የገለጹት አቶ ጌታቸው የክልሉ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ እንደሚሰራም አመልክተዋል።

"አንዳንድ አካላት ክልሉን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድርግ እየሰሩ በመሆኑ ሕዝቡ ሊጠነቀቅ ይገባል" ብለዋል።

ከአራት ሰዎች በላይ መሰብሰብ በማይቻልበት በአሁኑ ወቅት ኅብረተሰቡን ለችግር ለማጋለጥ የሚደረገውን ጥረት ሕዝቡ ተረድቶ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ጥሪውን የሚያቀርቡ ሰዎች የሽግግር መንግሥት ይመስረት የሚሉ አካላትና በአቋርጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ ኃይሎች መሆናቸውንና እነዚህም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም ኃይል የሚያበረታታና የሚደግፍ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም