ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ ከ100 ለሚበልጡ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረገች

ሆሳዕና፣ ግንቦት 22/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ወንጌላዊት መካነ እየሱስ ማዕከላዊ ደቡብ ሲኖዶስ የሆሳዕና አጥቢያ ቤተክርስቲያን በኮሮና ወረርሽን ምክንያት ለተቸገሩ ከ100 ለሚበልጡ አረጋዊያንና አቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉ በተሰጠበት ወቅት የማዕከላዊ ደቡብ ሲኖዶስ ፕሬዝዳንት አቶ አለሙ ጡሚሶ በአሁኑ ድጋፍ  በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎ ግራም የስንዴና የበቆሎ ዱቄት፣ፓስታ፣ ማካሮኒ፣ሩዝ ፣ የምግብ ዘይትና የንፅህና መጠበቂያ ሳሙና ተበርክቷል ብለዋል።

በዚህ  አስቸጋሪ ወቅት እርስ በእርስ በመደጋገፍና በመረዳዳት መሻገር እንደሚገባም አመልክተው  ቤተክርስቲያኗ ለሰው ልጆች ችግር ቅድሚያ በመስጠት ችግሩ እስኪቃለል ድረስ የሚጠበቅባትን እንደምታወጣም  ገልጸዋል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ የሆኑት የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሙላቱ ሱሌ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ  ላበረከተችው  አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል  ወይዘሮ አዳነች አብዮ  በመታመማቸው ምክንያት ረዳት አጥተው በተለይ በወረርሽኙ ምክንያት  በቤት ለመዋል በመገደዳቸው እንደተቸገሩ  ተናግረዋል።

የተደረገላቸው ድጋፍ  ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚረዳቸው በመግለጽ አመስግነዋል፡፡

አቶ ወርቁ በቀለ በበኩላቸው የቀን ስራ ሰርተው እናት የሞተባቸውን 12 ልጆች በማሳደግ ይተዳደሩ እንደነበር አውስተዋል።

ወረርሽኙ በሀገሪቱ መከሰትን ተከትሎ መንግስት ባወጣው መመሪያና በተሰጠው ግንዛቤ መሰረት እንደልብ ወጥተው  መስራት ባለመቻላቸው ከነልጆቻቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

ከባድ ፈተና ላይ ባሉበት ወቅት በተደረገላቸው ድጋፍ  መደሰታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም