የአሌልቱ ማረሚያ ማሰልጠኛ 1 ሺህ 179 የማረሚያ ቤት ፖሊሶችን አስመረቀ

57
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የአሌልቱ ማረሚያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ30ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 179 የማረሚያ ቤት ፖሊሶችን ትናንት አስመረቀ። ከተመራቂዎቹ መካከል 804ቱ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚሰማሩ ሲሆን 260ዎቹ በደቡብ ክልል ማረሚያ ቤቶች እንዲሁም 115ቱ በአፋር ክልል የሚሰሩ መሆናቸው ተገልጿል። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማል አባሶ  በስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለፁት፤ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ አገሪቱ የተያያዘችው ፈጣን ልማትና የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት እንዲኖረው ትልቅ ድርሻ አለው። ዋና ዳይሬክተሩ ተቋሙ የተለያዩ መልካም ተሞክሮዎችን ያካበተ ቢሆንም በህዝቡ ዘንድ የሚነሱ ክፍተቶች ሊታረሙ የሚገቡና በለውጥ ሂደቱ ለማስተካከል እየሰራን ነው ብለዋል። ተመራቂዎቹም የለውጡ ፈፃሚ አካል በመሆን የህግ ታራሚዎችንና ተገልጋዮችን በቀናነት በማገልገል ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል። የአሌልቱ ማረሚያ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ዋና ሱፐር ኢንተንደንት ሙላት ጫንያለው ሰልጣኞቹ ለ420 ሰዓታት የክፍል ውስጥ ትምህርትና ለ568 ሰዓታት የመስክ ስልጠና እንደወሰዱ ተናግረዋል። ተመራቂዎቹ በማሰልጠኛ ቆይታቸውም በበጎ አድራጎት ስራ ሲሳተፉ እንደቆዩ አንስተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ የኦሮሚያ ተወላጆች 119 ሺህ ብር ስጦታ፣ ከፍተኛ የጤና ችግር አጋጥሞት ከፍሎ መታከም ላልቻለ አንድ ግለሰብም 59 ሺህ ብር በማዋጣት እንዲታከም እንዳደረጉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም