የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ ተወሰነ

181

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2012  ዓ.ም ( ኢዜአ) የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከዛሬ ጀምሮ ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ ተወሰነ።

ሲሚንቶ አምራቾች ምርታቸውን ከታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም በፊት ሲሸጡ በነበረበት ዋጋ እንዲሸጡም ተብሏል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሲሚንቶ ኢንዱስትሪው ላይ በሚታዩ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ከአምራቾችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

በአምራቾችና ባለድርሻ አካላት በኩል የሲሚንቶ ኢንዱስትሪው ማነቆዎችና መፍትሄዎቻቸውን የተመለከቱ ሀሳቦች ቀርበዋል።

የሲሚንቶ የግብይት ሰንሰለት በደላሎች ቁጥጥር ስር ወድቋል፤ ይህም ምርቱ ተጠቃሚው ጋር ሲደርስ በከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጥ አድርጓል ብለዋል አምራቾችና ባለድርሻ አካላቱ።

ደላሎች የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን በመቆጣጠራቸው በኢኮኖሚው ላይ አሻጥር /ሳቦታጅ/ እየተፈጸመ ነው ሲሉም አንስተዋል።

አሁን ላይ አንድ ከረጢት ሲሚንቶ ከ300 እስከ 600 ብር እየተሸጠ መሆኑን በመግለጽ።

የንግድ ሰንሰለቱ ተዋናዮች በግልጽ ያልተለዩ ናቸው ሲሉም አመልክተዋል።

የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ በሆነው የትራንስፖርት አገልግሎት ውስጥም ደላሎች መሳተፋቸው ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት እንደሆነና ሲሚንቶው በተፈለገ ጊዜ ወደ ተጠቃሚው እንዳይደርስ ማድረጉን ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሮችም ምርቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዳይመረት እያደረጉ ስለመሆኑም በአምራቾችና ባለድርሻ አካላቱ ተነስቷል።

መንግስት ለችግሮቹ ተገቢውን መፍትሔ ይስጥ ሲሉም ጠይቀዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በሲሚንቶ ኢንዱስትሪው የግብይት ሰንሰለት ውሰጥ የሚገኙ ተዋናዮች በግልጽ አይታወቁም የተባለውን ተቀባይነት የሌለው ብለውታል።

"የሲሚንቶ አከፋፋዮችና የፋብሪካ ስራ አስፈጻሚዎች ቁርኝት አላቸው፤ ፋብሪካዎች ምርታቸውን እንዲያከፋፍሉ የሚፈልጉት ልዩ ትስስር ከፈጠሩባቸው አካላት ነው" በማለት።

በዚህ ሳቢያ በህጋዊ መንገድ ክፍያ የፈጸሙ አካላት የሲሚንቶ ምርት ለማግኘት ረጅም ጊዜ ሲወስድባቸው ህጋዊ ያልሆኑት ግን ምርቱ በአጭር ጊዜ እጃቸው እየገባ ነው ብለዋል።

ፋብሪካዎችና አከፋፋዮች "ያልተገባ የጥቅም ትስስር" ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰው ደላሎቹን ከግብይት ሰንሰለት ማስወጣት ያለባቸው ራሳቸው ፋብሪካዎቹ እንደሆኑ ተናግረዋል።

በሲሚንቶ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ግንባታዎች እየቆሙና ሠራተኞች እየተበተኑ መሆኑንና ይህም ስራ ፈጣሪውን የግንባታ ዘርፍ ህልውና መገዳደሩን ጠቅሰዋል ሚኒስትሩ።

የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያሏቸውን ከ1 ሺህ 800 በላይ አሽከርካሪዎች በአግባቡ ሳይጠቀሙ ተጨማሪ የትራንስፖርት አቅርቦት መጠየቃቸውም ተገቢነት የለውም ብለዋል። ተሽከርካሪዎቹ ከቀረጥ ነጻ መግባታቸውን በማስታወስ።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ መንግስት የሲሚንቶ ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ በየዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደርጋል።

ለሲሚንቶ ምርት ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ከሰል 220 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ እያደረገም ነው ብለዋል።

ከሶስት ሳምንት በፊት በተካሄደ ተመሳሳይ መድረክ አምራቾች ችግሩን እንዲፈቱ መጠየቁንና ይህን ካላደረጉ እርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹን አቶ መላኩ አስታውሰዋል።

በዚሁ መሰረትም መንግስት ችግሩን በጊዜያዊነት ይፈታሉ ያላቸውን ውሳኔዎች ማሳለፉን ገልጸዋል።

ከዛሬ ጀምሮ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሲሚንቶ እንዲያከፋፍሉ፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታም ወደ ስራው እንዲገቡ ተወስኗል ብለዋል።

የልማት ድርጅቶቹ ዋጋ መጨመር እንደማይችሉ የገለጹት ሚኒስትሩ የሲሚንቶ አቅርቦቱን ሳያጓትቱ በጊዜው ማድረስ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል።

አምራቾች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ለሌሎች የኃይል ማመንጫዎች የሚያቀርቡትን የሲሚንቶ ምርት በውላቸው መሰረት ማቅረብ እንደሚችሉም ገልጸዋል።

በግድቦች ላይ ከተቀመጠው ልዩ የማከፋፈል ሁኔታ በስተቀር አምራቾች ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ውጭ ምርታቸውን መሸጥ እንደማይችሉም ነው ያስታወቁት።

የልማት ድርጅቶች የሚኖርባቸውን የትራስፖርት፣ የሰው ኃይል፣ የጭነትና ሌሎች ወጪዎች ታሳቢ ያደረገ የትርፍ ህዳግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚወሰንም ገልጸዋል።

የልማት ድርጅቶቹ ሲሚንቶ ለቸርቻሪዎች የሚያቀርቡበትን ዋጋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚወስንም ነው አቶ መላኩ ያስረዱት።

የክልል መንግስታት ጉዳዩን በበላይነት እንዲያስተባብሩና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥማቸው ለሚኒስቴሩ ማቅረብ እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የኢንዱስትሪ ምርቶችና ግብዓቶች የሚሸጡበትን ዋጋ አስመልክቶ ተጨማሪ ውሳኔዎች እንደሚያስተላልፍም አክለዋል።

ውሳኔዎቹ የሲሚንቶ ዋጋ እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው በመጥቀስ።

በሲሚንቶ ኢንዱስትሪው ውስጥ በህገ ወጥ ተግባር የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ መንግስት ኃላፊዎችን በህግ ወደ መጠየቅና ፋብሪካዎችን ወደ ማሸግ እንደሚሄድም አስጠንቅቀዋል።

መንግስት የኤሌክትሪክ አቅርቦትና ሌሎች ዘርፉን እየተፈታተኑ ያሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ መፍትሄ እየሰጠ እንደሚሄድም ነው የተናገሩት።

በውይይቱ የተሳተፉ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ስራው ለመግባት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ኢንቨስትመንት ያቀፈው የሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ከ12 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ከኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም