ቀጥታ፡

በጨረታ ሰበብ 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ሲያጭበረብሩ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ደብረ ማርቆስ፣ ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ)  በደብረ ማርቆስ ከተማ የግዥ ጨረታ አሸንፈሃል በሚል ከአራት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ሲያጭበረብሩ የተደረሰባቸው ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አጃነው አዲስ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በተጭበረበረ ሰነድ ለመዝረፍ ሲሞክሩ ግንቦት 19 ቀን 2012 ዓ/ም በደብረ ማርቆስ ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ ነው።

ከተለያየ አካባቢ የመጡት ግለሰቦቹ የተያዙት በከተማ አስተዳደሩ በኮንስትራክሽን እቃዎች አቅርቦት ስራ የተሰማሩ አንድን  ግለሰብ በጨረታ ሰበብ ለማጭበርበር ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ግለሰቦቹ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሰራተኞች መስለው በመቅረብ ኮርፖሬሽኑ ለደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ቡሬ ካንፓስ ህንጻ  ግንባታ የሚውል ብረት ጨረታ እንዲሳተፉ ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ባለሃብቱ የ4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ፐርፎርማ እንዲሞሉ ያደርጋቸዋል ።

ከጥቂት ቀናት በኋላም ባለሃብቱ ጨረታውን እንዳሸነፉና በደብረ ማርቆስ ከተማ መጥተው ውል እንዲፈፅሙ ጥሪ ያደርጉላቸዋል ።

ጨረታውን እንዳሸነፉ የተነገራቸው  ግለሰብ የጠቅላላ ዋጋውን ሁለት በመቶ እንዲከፍሉ ከገለፁላቸው በኋላ በጉዳዩ ጥርጣሬ ስላደረባቸው ለፖሊስ በመጠቆም እጅ ከፍንጅ እንዲያዙ አድርገዋል ።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅትም በኮርፖሬሽኑ ስም የተጭበረበረ የንብረት ገቢ ደረሰኝ፣ የፕሮፎርማ ሰነድ፣የራስጌ እና የግርጌ ማህተም፣ የስልጣን እና የስም ቲተር ተገኝቶባቸዋል።

እንዲሁም የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ፣ የአሸናፊነት ደብዳቤ የያዘ ሰነድ እና የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞች ለመሆናቸው የሚገልጽ የተጭበረበረ መታወቂያ የተገኘባቸው መሆኑንም ዋና ኢንስፔክተሩ አብራርተዋል።

ግለሰቦቹ ከዚህ በፊትም ሌሎችን ያታልሉ እንደነበር ጠቅሰው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሁለት ግለሰቦች ቀርበው የማጭበርር ሙከራ እንደተደረገባቸው ማመልከታቸውን ገልፀዋል።

ካመለከቱት አንደኛው የቤት እና የቢሮ እቃዎች አቅራቢ ድርጅት ባለቤት ሲሆኑ ለስድስት ኮሌጆች የቢሮ እቃ በ7 ሚሊየን ብር ወጭ መግዛት ስለምንፈልግ  ጨረታ ሙላ ብለው ሰነድ እንዳቀረቡላቸው ገልፀዋል ።

የቀረበው ሰነድ የተስተካከለ ባለመሆኑ እንዲስተካከል ሲጠይቁዋቸው አስተካክለን እንመለሳለን ብለው እንደሔዱ በዚያ መቅረታቸውን ለፖሊስ ተናግረዋል ።

ኮምፒዩተር አቅራቢ ድርጀት ለሆኑት ሌላ ግለሰብም የበጎ አድራጊ ድርጅት ሰራተኞች መስለው በመቅረብ ለአዊ፣ ለጎንደር እና ሌሎች  6 የመንግስት ኮሌጆች ኮምፒተር ልናቀርብ ነው በማለት የሰነድ መሙያ አንድ ሺህ ብር እንደተቀበሉዋቸው ተናግረዋል ።

በቀጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ጉዳያቸውን የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተሩ ጠቅሰው መሰል የማጭበርበር ችግር የገጠማቸው ሰዎች ካሉም  ለፖሊስ እንዲያመለክቱ ጥሪ አቅርበዋል ።

ህብረተሰቡ ከመሰል የማጭበርበር ስልቶች መጠንቀቅ እንዳለበት ጠቅሰው፤ በተለይም ነጋዴዎች የግዥ ጨረታዎች ህጋዊነት ማረጋገጥ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም