ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለከፊል አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር እና የእርሻ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ

101

ሐረር፣ ግንቦት 21/2012 ( ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቁንቢ ወረዳ ለሚገኙ 100 ከፊል አርሶ አደሮች ምርጥ ዘር እና የእርሻ መሳሪያ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ በወረዳው ሚኖ ቀበሌ በተሰጠበት ወቅት የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ዶክተር አብዱለጢፍ አህመድ እንዳሉት ተቋሙ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የምርምር፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናና የግብአት ድጋፍ እያደረገ ነው።

በአሁኑ ወቅትም  በቁንቢ ወረዳ ለ100 ከፊል አርሶ አደሮች  ባላቸው ሰፊ ማሳ ላይ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማገዝ ምርጥ ዘር እና እርሻ መሳሪያ  አከፋፍለዋል።

የተከፋፈሉት እነዚህ  የበቆሎ፣ቦሎቄ፣ እና ማሽላ ምርጥ ዘር የዝናብ እጥረትና  በሽታን  ተቋቁመው  በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ መሆናቸው ገልጸው፤ ለምርጥ ዘሩና የእርሻ መሳሪያ  ከ300ሺ ብር በላይ  ወጪ ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

የቁንቢ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሐምዲ መሀመድ በበኩላቸው  ዩኒቨርሲቲው ያደረገው የምርጥ ዘርና የእርሻ መሳሪያ ድጋፍ የከፊል አርሶ አደሩ በምግብ እራሱን እንዲችል እና የግብርና ስራውን ለማጠናከር  እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው  መካከል አቶ ጀማል ዱሪ "ድጋፉ የጀመርነውን የግብርና ስራ ለማሳደግ እና እራሳችንን በምግብ እንድንችል እገዛ ያደርግልናል " ብለዋል።

ሩቢያ ሼህ መሀመድ ዩኒቨርሲቲው የሰጣቸው ምርጥ ዘር ባዛጋጁት  ማሳ ላይ በመዝራት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም