ቀጥታ፡

ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ አገኘ

አዲስ  አበባ  ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር ለኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የተገመቱ ቁሳቁሶችን አበረከተ።

ማኅበሩ ያበረከተው 30 ዊንዶውስ ታብሌት ኮምፒውተሮች፣ ሶስት አንድሮይድ ታብሌት ስልኮች እንዲሁም ለ400 የጤና ባለሙያዎች አልባሳት፣ የቀዶ ሕክምና ቀሚሶችና ቦት ጫማዎችን ነው።

የማኅበሩ ሊቀ መንበር ካፒቴን በረከት አባተ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን የመተጋገዝ ጥሪ ተከትሎ ከአባላቱና ከማኅበሩ በተገኘው ገንዘብ ለሕክምና ባለሙያዎች ይሆናሉ ያሏቸውን ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የአገሪቷ የኢኮኖሚ አቅምና ሁኔታ መረዳዳትና መደጋገፍ ካልታከለበት ወረርሽኙን አሸንፎ ለመሻገር አስቸጋሪ መሆኑን መረዳታቸው ድጋፉን ለማድረግ እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

ወረርሽኙ ተሻጋሪና እስከ መቼ እንደሚቆይ እንኳን የማይታወቅ በመሆኑ ሁሉም አብራሪዎች አገራቸውና አየር መንገዱ የሚያቀርቡትን ጥሪ በመቀበል ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ያሬድ አግደው ለሆስፒታሉ ከመንግስትና ከተለያዩ ድርጅቶች ድጋፎች እንደሚደረጉ አውስተው የአውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር በተደራጀ መልኩ ድጋፍ በማድረግ ቀዳሚ መሆኑን ገልፀዋል።

የተደረጉት ድጋፎች የጤና ባለሙያዎች አስፈላጊ አልባሳትን አሟልተው ቫይረሱ ለተገኘባቸው ሰዎች ተገቢውን ክትትል ለማድረግ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ግብዓቶቹም ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ በመሆኑ የጤና ባለሙያው የሚወጡ አዳዲስ መመሪያዎችን እንዲከተል እንደሚረዱም አክለዋል።

በመንግስት ብቻ የሚሰጡ ድጋፎች በቂ አለመሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ያሬድ መሰል ድጋፎች አገልግሎቱን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛሉ ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡም አሁን የሚያሳየውን ፍርሃትና መዘናጋት በማስወገድ ከመንግስትና ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበር በጤና ባለሙያው ላይ ያለውን ጫና እንዲቀንስ ጥሪ አቅርበዋል።

አብራሪዎቹ ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ አየር መንገዱ የሚያጋጥመውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማቃለል እየሰሩ ከመሆናቸው ባሻገር ለተለያዩ አገራት የሕክምና ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ተነግሯል።

ከተመሰረተ 50 ዓመታትን የተሻገረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች ማኅበር በበረራ ደህንነት፣ በአብራሪዎች ሙያዊ ብቃትና መብት ላይ እየሰራ ያለና ከ800 በላይ አባላት ያሉት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም