የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ የወጡ መመሪያና ስምምነቶችን የሚጥሱ ሆቴሎች ሊታረሙ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ የወጡ መመሪያና ስምምነቶችን የሚጥሱ ሆቴሎች ሊታረሙ ይገባል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 21/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሆቴሎች ባለሙያዎች ማኅበር ኮቪድ-19ን ምክንያት በማድረግ ሠራተኛ እና ደመወዝ እየቀነሱ ያሉ አንዳንድ ሆቴሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠየቀ።
ወረርሽኙን ተከትሎ የወጡ መመሪያና ስምምነቶችን እንዲያከብሩም ጠይቋል።
ማኅበሩ በሆቴል ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች አስቸጋሪውን ጊዜ በመተሳሰብ እንዲያልፉም ነው ጥሪ ያስተላለፈው።
አንዳንድ ሆቴሎች ሠራተኞችና ደመወዝ እየቀነሱ መሆኑን፣ ከስራ የተሰናበቱና የታገዱም ስለመኖራቸው ማኅበሩ በከፈተው የማኅበራዊ ትስስር ገፅ /ቴሌግራም/ ቅሬታዎች እየቀረቡ እንደሆነ አስታውቋል።
ባለው መረጃ መሰረት 14 ሆቴሎች ላይ ከሠራተኞቻቸው ቅሬታ እንደቀረበባቸውና ከነዚህ መካከል በሰባቱ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደተፈቱ ገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ልዑልሰገድ መሰለ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ትልቅ ጫና ቢያሳድርም መንግስት ዘርፉን ለመታደግ ለወሰዳቸው እርምጃዎች አመስግነዋል።
በማኅበሩ በተደረገ የዳሰሳ ጥናትም ከ90 በመቶ በላይ ዘርፉ መጎዳቱን ቢያመላክትም በመንግስት የተደረጉ እንደ ገቢ ግብር ቅነሳና ብድር ማራዘም እርምጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
የዘርፉ ባለሙያዎች በዚህ ወቅት ተባብረው ጊዜውን መሻገር እንጂ የደመወዝ ቅነሳና ሠራተኛን የማባረር ድርጊቶች መፈጸም የለባቸውም ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በርካታ ሆቴሎች ጊዜውን አብረን እንሻገራለን በማለት በመደበኛ አካሄዳቸው መቀጠላቸውን አድንቀዋል።
ኮቪድ-19ን ተከትሎ የወጡ መመሪያና ስምምነቶችን ባለ ማክበር ሠራተኛ ከመቀነስ ባሻገር ቫይረሱን መከላከያ ግብዓቶችን የማያቀርቡ አንዳንድ ሆቴሎች እንዳሉ የገለጹት ደግሞ የማኅበሩ የቦርድ አባል አቶ ይታሰብ ስዩም ናቸው።
ይህን ድርጊት ፈጽመዋል የተባሉ ሆቴሎችን ስም ከመጥቀስ ቢቆጠቡም ከመሰል ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።
እስከ 50 በመቶ ደመወዝ የቀነሱ ሆቴሎች መኖራቸውን በማንሳት የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ የወጡ መመሪያና ስምምነቶች አተገባበር ላይ ክትትል እንዲደረግም ነው ማኅበሩ የጠየቀው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እስከ 70 በመቶ ገቢያቸው ከደንበኞች ከሚሰበሰብ ሰርቪስ ቻርጅ መሆኑና የሆቴሎች ስራ መቀነስ በሠራተኞች ገቢ ላይም ተፅዕኖ ማሳደሩ በማኅበሩ መግለጫ ተጠቁሟል።
በመሆኑም መንግስት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሠራተኞች ነፃ ትራንስፖርት በማቅረብና ከሆቴሎች የተቀነሰው የገቢ ግብር ለሠራተኛው እንዲከፈል በማድረግ ዜጎቹን እንዲደግፍም ጥሪ ቀርቧል።
ማኅበሩ ኮሮና ቫይረስ በዘርፉ ላይ እያደረሰ ያለውን ተፅዕኖና የማገገሚያ ስትራቴጂዎች ያካተተ አገር አቀፍ ጥናት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እያካሄደ መሆኑም ተገልጿል።