በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር ሊሆን ይገባል- የህግ ባለሙያዎች - ኢዜአ አማርኛ
በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር የሀገሪቱን ጥቅም የሚያስከብር ሊሆን ይገባል- የህግ ባለሙያዎች
ሶዶ/ሰመራ/ ግንቦት 21/2012 (ኢዜአ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረግ ቀጣይ ድርድር የሃገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም በሚያስከብር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ በወላይታ ሶዶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ ባለሙያዎች ተናገሩ ፡፡
በሌላ በኩል ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በአፋር ክልል የሰመራ-ሎግያ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲንና መምህር አቶ ተከተል ለቤና እንዳሉት በግድቡ ግንባታ ላይ የሶስትዮሽ ስምምነቱ ላይ ለማደራደር ቀርባ የነበረችው አሜሪካም ከገለልተኝነቷ ይልቅ ለግብፅ ወግናለች።
ጉዳዩ የአፍሪካ እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረት እንደ አደራዳሪ ሊሆን እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ተከተል "ወደ ድርድሩ መመለስ ግዴታ ቢሆን እንኳን የሃገሪቱ ብሔራዊ ጥቅም በጥንቃቄ መታየት ይገባዋል" ብለዋል።
ግብፅ ወደ ድርድሩ ለመመለስ መስማማቷን እንደማይደግፉ የገለጹት ደግሞ በወላይታ ሶዶ የህግ አማካሪና የግል ጠበቃ የሆኑት አቶ ሰይፉ አላሮ ናቸው።
ካሁን በፊት ባሳየችው የአቋም መቀያየር ምክንያት ግብፅ እምነት ሊጣልባት የማይገባ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለያየ ጊዜ ለድርድር ቀርባ ከፈረመች በኋላ በሃሳቧ አለመፅናቷን ተከትሎ አሁንም የመጣችበት ዓላማ በድርድር ሰበብ የውሃ ሙሌቱን ለማጓተት ሌላ ማዘናጊያ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ጥርጣሬ ገልጸዋል።
በአባይ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያን በመወከል ድርድሩ ላይ የሚቀርቡ አካላት ኢ-ፍትሃዊ የሆነን ሀሳብ መመከት የሚያስችል መደራደሪያ ይዘው በመቅረብ የሃገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማይነካ መልኩ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የግድቡ ውሀ ሙሌት በአባይ ውሃ ላይ ጥቅም ያላቸውን ሌሎች ሃገራትን የማይጎዳ መሆኑን ማስረዳትም በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
"ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊም ሆነ ህጋዊ መብት አሳልፎ በሚሰጥ ማንኛውም ጉዳይ ላይ መደራደር የለባትም " ያሉት ደግሞ የዳሞት ጋሌ ወረዳ አቃቤ ህግ አቶ ዘውድነህ ደስታ ናቸው።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስራን ለማጓተት የአንዳንድ ሃገራት ጣልቃ ገብነት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ለህዳሴው ግድብ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ በአፋር ክልል ሰመራ-ሎግያ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ዮሃንስ መኮንን የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከደመወዛቸው በመቀነስ ቦንድ በመግዛት እንደ ዜጋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አውስተዋል።
በቀጣይም የግድቡ ግንባታ ከፍጻሜ እስኪደርስ ድረስ ቦንድ በመግዛትም ሆኑ እስከ ህይወት መስዋእትነት እንደሚከፍሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተለይም ግብፅ በአባይ ወንዝ ጉዳይ የምታራምደውን ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ለማክሸፍ በአንድነት መቆም አለብን ብለዋል።
ወይዘሮ አስቴር ይልማ በበኩላቸው "ሀገራችን ከአባይ ወንዝ ለመጠቀም የጀመረችው የህዳሴው ግድቡ ግንባታ እስሚጠናቀቅ ድረስ ከመንግሰት ጎን በመቆም እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ ለመክፍል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
"ለዚህ ፕሮጀክት እውን መሆን ሁሉም ኢትጵያዊያን ያለምንም ልዩነት በጋራ በሀሳብም ሆነ በገንዘብ ድጋፋችንን በመስጠት ግንባታውን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ አድርሰናል " ያለው ደግሞ ወጣት አህመድ መሃመድ ነው።
ይሄው ድጋፍ ግለቱን ጠብቆ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁሟል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አብደላ መሃመድ የመንግስት ሰራተኛ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ አሁን በተሰማሩበት የግል ስራው ከሚያገኙት ገቢ በመቀነስ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ድጋፋቸውን እስከ መጨረሻው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።