በጋሞ ዞን በመሬት ናዳ የ10 ሰዎች ሕይወት አለፈ

61

አርባምንጭ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) በጋሞ ዞን በጋጮባባ ወረዳ ጋፀ እና ግና በሚባሉ ሁለት ቀበሌዎች ዛሬ በተከሰተ የመሬት ናዳ የ10 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የዞኑ ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ሬታ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው ዛሬ ጠዋት የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተ ነው።

በአደጋው ከሞቱት ሰዎች መካከል የስድስቱ አስከሬን የተገኘ ሲሆን የአራቱ ሰዎች ገና በሰው ኃይል ቁፋሮ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አካባቢው ተራራማ በመሆኑ የመኪናው መንገድ በናዳ የተዘጋ ስለሆነ ዶዘር ማስገባት አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

በዚሁ ምክንያት የጋሞ ዞን ፀጥታ ኃይሎችና የአመራር አካላት በእግር ተጉዘው በሥፍራው በመድረስ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአደጋው የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛትና የንብረት ውድመት መረጃ እየተጣራ እንደሚገኝም ኮማንደር ሬታ ተክሉ ጠቁመዋል።

የዛሬውን ሳይጨምር በያዝነው ዓመት ብቻ በአካባቢው በተከሰተ የመሬት ናዳ 12 ሰዎች መሞታቸውን መዘገቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም