ጊዜና ወረርሽኝ የማይገድበው የተፈጥሮ እውነት

53

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረውን የሴቶች የወር አበባ ቀን መቀላቀሏን የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት አድን ድርጅት አስታወቀ።

እለቱ የተከበረው የወር አበባ በወረርሸኝ ወቅት ተግባራዊ ምላሽ የሚጠይቅበት መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ነው።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ አስፈላጊነትን በማስገንዘብ ሴቶችንና ልጃገረዶችን መደገፍ የሚለው በዘንድሮው አከባበር ትኩረት እንደተሰጠው ተገልጿል።

በተለይ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ፣ በአገር ውስጥ መፈናቀል የገጠማቸው፣ ስደተኞች፣ በለይቶ ማቆያ  የሚገኙና በትራንዚት ማዕከላት የሚገኙ ልጃገረዶናችና ሴቶች ልዩ ትኩረት ያሻቸዋል ተብሏል።

ሴቶች በዚህ ፈታኝ ወቅት የሚደረግላቸው ድጋፍ ክብራቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው ዩኒሴፍ ያወጣው መግለጫ ያሳያል።

ኮቪድ-19 እና መሰል ወረርሽኞች ሴቶችና ልጃገረዶች እንዲሁም ወረርሽኙን ለመታገል ግንባር ቀደም ሆነው የተሰለፉ ሴቶች የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ ቁሶች ለማቅረብ እንደማይገደቡ ተገልጿል።

“በዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ዓለም አቀፍ የወር አበባ ንጽህና ቀንን ስናከብር የንፅህና መጠበቂያዎች ሳሙና እና ውሃ የሴቶች እና የልጃገረዶች መሠረታዊ መብቶች መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፤ የወር አበባ ንጽህና አጠባበቅ በትምህርት ቤት ውስጥ ከሴቶች ስኬት፣ በራስ መተማመን እና ክብር ጋር የተዛመደ ነው" በማለት የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ እለቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መለዕክት ተናግረዋል።

"የወር አበባ ዑደትን ለማስተዳደር አስፈላጊ መረጃዎችን እና መገልገያ አቅርቦቶችን መስጠት የቅንጦት ሳይሆን ወሳኝ ፍላጎት ነው” በማለትም ሚኒስትሯ አክለዋል።

ፍሬወይኒ መብራሃቱ በሲ.ኤን.ኤን የአመቱ ጀግና ተብላ የተመረጠቸው በአገሪቱ ገጠራማ ክፍል የወር አበባን ተከትሎ ያለውን የተዛባ ባህላዊ አመለካከትና ማግለል ለመቀነስ በሰራችው ሥራ ነው።

በኢትዮጵያ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂነት የተቋቋመው "የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅና የጤና ግብረሃይል" የወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ፕሮግራምን ተደራሽ ለማድረግ የተዋቀረ ነው።

የዩኒሴፍ መግለጫው እንደሚያሳየው በርካታ ሰዎች የጉዳዩን አሳሳቢነት ፈጽመው ካለመረዳት ባለፈ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች አሁንም የንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን በቀላሉ ማግኘት እንደማይችሉ አያውቁም።

በዚህ የተነሳ በርካታ ሴቶች ንፅህናው ያልተጠበቀና ለጤና አደገኛ የሆኑ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ለመጠቀም እንደሚገደዱ ከዩኒሴፍ ጋር አብረው የሚሰሩ ልጃገረዶች መናገራቸው ተገልጿል።

ዩኒሴፍ እኤአ በ2020 ባደረገው ምልከታ 18 በመቶ የሚጠጉ ወጣት ሴቶች የወር አበባ በሚመጣባቸው ወቅት ትምህርት እንደሚያቋርጡ አረጋግጧል።

የዩኒሴፍ ተወካይ አዴል ኮዶር ዩኒሴፍ ከመንግስታትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ሴቶችና ልጃገረዶች የተፈጥሮ ግዴታቸውን በሚወጡበት ወቅት ያልተገባ ነገር እንዳይገጥማቸው እየሰሩ መሆናቸውን  ተናግረዋል።

በተለይ በትምህርት ቤቶችና በጤና ማዕከላት "ዋን ወሽን" ከመሰሉ አጋር ድርጅቶችና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ የተጠናከረ ሥራ በመሰራት ላይ መሆኑን ነው ተወካዩ የጠቆሙት።

ከእንግሊዝ፣ ኔዘርላንድስ እና ካናዳ በተገኘ ድጋፍ ለ106ሺህ ተማሪዎችና ለ13 ሚሊዮን ዜጎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መሰጠቱን ጨምረው ተናግረዋል።

መንግስት ከዩኒሴፍ ጋር በመሆን በሴቶች ላይ የሚደርሰው መገለል እንዲቆም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በበረታበት በዚህ ወቅት የችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችንና ልጃገረዶችን መደገፍ እንደሚገባ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም