ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች የኮቪድ-19 መከላከያ ድጋፍ ተደረገ

59

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 20/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የኮቪድ- 19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓቶችን ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ለግሷል።

በትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ የተመራ የፌዴራልና የሶማሌ ክልል የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን ተወካዮችን ያካተተ ልዑክ በኢትዮ-ጅቡቲ  ድንበር የምትገኘውን ደወሌ ኬላ ተመልክቷል።

በዚህ ወቅትም 700 ሺህ ብር የሚገመት የኮቪድ 19 መከላከያ ግብዓት በፌዴሬሽኑ በኩል ተለግሷል።

ልገሳው 20 ሊትር ሳኒታይዘር፣ 10 የሙቀት መለኪያዎች፣ 500 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ከ16 ሺህ ሊትር በላይ የሚይዙ ሁለት የውሃ መያዣ ሮቶዎችና 4 ሺህ ሊትር የመኪና ማፅጃ ኬሚካልና ሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ግብዓቶች በኢትዮጵያ ትራንስፖርት ባለስልጣን በኩል ተበርክቷል።

ግብዓቶቹም የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ራሳቸውን ለመጠበቅና የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል።

የልኡካን ቡድኑ ከድሬዳዋ ጀምሮ በአይሻ ደወሌ እስከ ጅቡቲ በሚያዘልቀው መስመር በጉብኝት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም