ምሁራን፣ አትሌቶችና አርቲስቶች በኦሮሚያ ክልል የግብርና ልማት ስራዎችን ጎበኙ

133

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2012 (ኢዜአ) ምሁራን፣ አትሌቶችና አርቲስቶችን የያዘ ልዑካን ቡድን በኦሮሚያ ክልል የግብርና ልማት ስራዎችን ዛሬ ጎብኝቷል። 

የልዑካን ቡድኑ በምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ እና አዳማ ወረዳዎች በሚገኙ የችግኝ ጣቢያዎች የሚሰሩትን ስራዎች ጎብኝተዋል።

በተጨማሪም በመቂ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን በወጣቶች እየለማ የሚገኝ  2 ሺህ ሄክታር የፓፓያ ልማት ክላስተርን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል።

በዱግዳ ወረዳ በ2 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ በሚያዘጋጀው ፍሎራዜ ችግኝ ጣቢያ ተገኝተው እየተካሄደ ያለውን ልማት ጎብኝተዋል።

የችግኝ ጣቢያው ባለቤት አቶ በየነ ያለው እንደተናገሩት፤ ጣቢያው በየዓመቱ 70 ሚሊዮን የሚሆን የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ በማልማት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢ ያሰራጫል።

የፓፓያ ክላስተሩን በተመለከተ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የግብርና ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ ለወጣቶቹ ገበያ የማመቻቸት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው እየተካሄደ ያለው የግብርና ልማት ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የክልሉ እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌ በግብርና ዘርፍ ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ ተሰማርተው የነበሩ 105 አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስተርነት መሸጋገራቸውም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም