ቀጥታ፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ ተጨባጭ ድጋፍ አላደረጉም

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ)  በኢትዮጵያ የሚገኙ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጨባጭ ድጋፍ አለማድረጋቸው ተነገረ።

ወቅቱ ፓርቲዎቹ አገራዊ አንድነታቸውን በተግባር የሚያሳዩበት እንደሆነም ተጠቁሟል። 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ያዘጋጁት የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሂዷል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ሙሳ አደም በዚሁ ጊዜ እንተናገሩት የግድቡ ግንባታ ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ ለፖለቲካዊና ማኅበራዊ መስተጋብር መጠናከር የጎላ ሚና አለው።

ፓርቲዎች የፖለቲካ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ከሚይዙባቸው ጉዳዮች የሕዳሴው ግድብ ዋነኛው ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶች አገራዊ አንድነታቸውን ከቃላት ባለፈ በተግባር የሚያሳዩበት ጊዜ አሁን ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ ከአገር ሉዓላዊነት በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አይኖርም ብለዋል።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ በተጨባጭ ያደረጉት ድጋፍ አለመኖሩንም ነው አቶ ሙሳ የገለጹት።

'የዛሬው ውይይት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገራችን የሚኖረን አስተዋጽኦ ለስልጣን ከመወዳደርና የመንግስትን ክፍተቶች እየተከታተልን ከማሳየት ባሻገር በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አንድ መሆን አንደምንችል ያሳየንበት ነው' ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለምክር ቤቱ አባላት ስለ ሕዳሴው ግድብ የዲፕሎማሲና የቴክኒክ ስራዎች ገለጻ አድርገዋል።

አቶ ገዱ በገለጻቸው የሕዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ አጀንዳ መሆኑን ነው ያነሱት።

ግድቡ ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት በ'ይቻላል' መንፈስ የምታከናውነው ወሳኝ ፕሮጀክት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ከግድቡ ግንባታ ጋር የተጀመረው የዲፕሎማሲ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ውሃውን ሙሉ ለሙሉ ለመጠቀም ባላቸው ፍላጎት ሊቀበሉት እንዳልቻሉ አብራርተዋል።

የተፋሰሱ አገራት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ሲቀር በውሃ ሙሌቱ ላይ አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣት በዲፕሎማሲ ስራው ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆኑን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት የትኛውም ሃይል ሊያስቆማት እንደማይችል የገለጹት አቶ ገዱ፤ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የግድቡን ግንባታ አሁናዊ ሁኔታ ሲያብራሩ በመጪው ሐምሌ ውሃ መያዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ ልዩነቱን ረስቶ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 73 በመቶ የደረሰ ሲሆን በመጪው ሐምሌ ውሃ መያዝ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም