ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣዩ በጀት ዓመት አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች አትጀምርም

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 ኢትዮጵያ በ2011 በጀት ዓመት አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች እንደማትጀምር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ቀደም ሲል የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ብለዋል። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፤ በቀጣዩ በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ቀደም ብላ የጀመረቻቸውን ፕሮጀክቶች ለመጨረስ ትኩረት ታደርጋለች ብለዋል። አሁን ባለው የፕሮጀክቶች አፈጻጸም አገሪቱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ከውጭ ምንዛሪ አኳያ አዋጭ አለመሆኑን የገለጹት፤ የፕሮጀክቶችን ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ መጀመሪያ በዕውቀትና በፋይናንስ አመራር ፕሮጀክቶችን መፈጸም እንደሚገባ ተናግረዋል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች 400 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ ባንኮች እንደተበደሩ የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን በርካታ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እየተጠናቀቁ አይደለም። በዚህም አንዳንድ የልማት ድርጅቶች ካላቸው አጠቃላይ ሀብት የሚስተካከል አልያም ከሃብታቸው የሚልቅ ዕዳ እንዳለባቸው ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከንግድ መርህ አንጻር ይህ አዋጭነት የለውም" ነው ያሉት። በተለይም በስኳርና በማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በኩል ጊዜው ስኳር ተመርቶ ለገበያ ቀርቦ ገቢ የሚደረግበት ወቅት ነበር ብለዋል። ስለሆነም ተጨማሪ ጊዜና ሀብት እየወጣባቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፣ የልማት ድርጅቶቹ መስራት የሚችሉት እንዲሰሩ፣ የማይችሉትን ደግሞ ወደግል ዘርፍ እንዲያሸጋግሩ በማድረግ በሚቀጥለው ዓመት አብዛኞቹን ለማጠናቀቅና ወደ ስራ ለማስገባት ታስቧል ነው ያሉት። ከዚህ በኋላ ከሚገኘው ሀብት ጨምረን በተሟላ ዕውቀት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ መገንባት እንሸጋገራለን ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም