በትግራይ ሁለት የአስፓልት መንገድ ፕሮክቶች ግንባታ ተጓተተ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ሁለት የአስፓልት መንገድ ፕሮክቶች ግንባታ ተጓተተ
ማይጨው/አክሱም ግንቦት 19/2012(ኢዜአ) በትግራይ ክልል 3 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ ለመገንባት የተጀመሩ ሁለት የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተታቸው ተገለጸ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እንዳመለከተው የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ከዓዲሸሁ ዴላ ሳምረና ከዓድዋ ራማ የሚያገናኙ ከ116 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው ናቸው።
ከእነዚህም በደቡባዊ ዞን ሁለት ቢሊዮን 200 ሚሊዮን ን ብር ወጪ ለመገንባት በግንቦት ወር 2011ዓ.ም የተጀመረው የአዲሽሁ -ደላ-ሳምረ የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው።
በባለሥልጣኑ የሰሜን ሪጅን ኮንስትራክሽን ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሁሉንአየው ወጂ ለኢዜአ እንደተናገሩት የመንገዱ ግንባታ በሶስት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታቅዱ ነበር።
በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ተቋራጭ የተጀመረው የአስፓልት መንገዱ 76 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው።
የመንገድ ግንባታ በቅዱ መሰረት አሁን ላይ 10 በመቶ መድረስ ሲገባው ከሶስት በመቶ አለመዝለሉን አመላክተዋል።
ተቋራጩ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ነዳጅና ሌሎች ግብአቶች በጊዜው ለማቅረብ ባለመቻሉ የተጓተተው ግንባታ አሁን ችግሩ እየተፈታ በመሆኑ አፈጻጸሙ ለማሻሻል ድጋፍ እያደረግን ነው ብለዋል።
በመከላከያ ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ የግብአት አቅርቦት ኬዝ ቲም መሪ ሻምበል ኤርምያስ ራንጓ በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታው በወቅቱ ቢጀመርም በነዳጅ ችግርና በጀት በወቅቱ ባለመቀቁ መዘግየቱን ገልፀዋል።
አሁን ላይ የሠራተኞች ደመወዝና የነዳጅ ችግር በመፈታቱ ስራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
መንገዱ አላጀ፣ ሰልዋና ሳምረ ወረዳዎች በማገናኘት ለዘመናዊ ትራንስፖርትና ልማት ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተናገሩት ደግሞ የአላጀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ብርሀኑ ናቸው።
መንገዱ አሁን እየተሰራበት ባለው የተጓተተ አካሄድ በተያዘለት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ ከባድ እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ የወረዳው አርሶአደር ዮዕብዮ ሓዱሽ ናቸው።
በተመሳሳይ ዓድዋ ራማ ከተማ 40 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአስፓልት መንገድ ግንባታ በሶስት ዓመታት ለማጠናቀቅ እቅድ እንደተያዘ በበላስልጣኑ የሰሜን ሪጅን ኮንስራክሽን ፕሮጀክቶች ማነጅመንት ዳይሬክተር አቶ መልካ በቀለ ገልጸዋል።
807 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ ለመገንባት በ2010 ዓ.ም የተጀመረው የመንገዱ ግንባታ አፈጻጸም ከ40 በመቶ እንዳላለፈ አመልክተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት በተቋራጩ ችግርና ወሰን ማስከበር መዘግየት የመንገዱ አፈጻጸም በተያዘለት ጊዜ እየተጓዘ አለመሆኑን አስረድተዋል።
የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ለማሻሸል ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ገልጸው ተቋራጩ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜም ማነጅመንቱና አማካሪው ውይይት እያደረጉበት ነው ብለዋል።
የዓድዋ ራማ መንገድ ተቋራጭ አፍሮ ጽዮን የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ዘመንፈስ ኪዳነ በበኩላቸው ለአስፓልት ንጣፍ የሚሆን ግብአት በወቅቱ ባለመገኘቱ ለመጓተቱ አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን ግብአቱ በመሟላቱ በሚቀጥለው ሰኔ ወር አስፓልት የማንጠፍ ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
ሁለቱም የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ፈጥነው በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተቋራጮቹ ገልጸዋል።
,
or