ቀይ መስቀል ማኅበር ለ400 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ቀይ መስቀል ማኅበር ለ400 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ አደረገ
ነገሌ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በነገሌ ከተማ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ 400 አቅመ ደካሞችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ አደረገ።
በማኅበሩ የነገሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ይርዳው ደግነህ እንደገለጹት ያደረጉት ድጋፍ የቀንና የሌሊት አልባሳት፣ የምግብ እህል፣ ማብሰያና የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ናቸው።
ድጋፍ የተደረጋላቸው ወገኖች በኮሮና ቫይረስ ሥጋት መሥራት ያልቻሉና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እንደሆኑ አመልክተዋል።
የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የነገሌ ከተማ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታምሩ ታዬ በበኩላቸው "በማኅበሩ የተደረገው ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል" ብለዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ መሊቻ ሀለኬ በሰጡት አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ከመምጣቱ በፊት በችርቻሮ ንግድ አንዳንዴም በቀን ሥራ ቤተሰቦቻቸውን ያስተዳድሩ እንደነበር አውስተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቫይረሱን በመፍራት ሥራቸውን በአግባቡ ማከናወን ባለመቻላቸው ገቢያቸው በመቀነሱ ምክንያት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
የተደረገላቸው ድጋፍ የራሳቸውንና የቤተሰቦቸውን ችግር ለማቃለል እንደሚረዳቸው በመግለጽ ምሥጋና አቅርበዋል።
ሌላው የነገሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኪዮ ኢብራሂም በበኩላቸው እንጀራ ጋግረው በመሸጥ ስምንት ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያስተዳደሩ ገልጸዋል።
የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ሥጋት በኑሮቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው ጠቁመው "ድጋፉ የመረዳዳት ባህልን የሚያጠናክር ነው" ብለዋል።