ተጨማሪ 46 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
ተጨማሪ 46 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው፤ የአንድ ሰው ህይወት አለፈ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 3410 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 46 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸውና የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
በዚህም እስካሁን በሀገሪቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 701 ደርሷል።
ሚኒስትሯ እንደገለፁት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጠው እድሜያቸው ከ12 እስከ 79 ዓመት የሆኑ 29 ወንድና 11 ሴት ሲሆኑ ከነዚህ መካከል 45ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 13 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆን 4 ሰው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው፣ አንድ ሰው የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያለው እንዲሁም 8 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነትም ሆነ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው።
ሶስት ሰዎች ከትግራይ ክልል ሁሉም የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው እና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ፣ 15 ሰዎች ከአማራ ክልል ሁሉም የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸውና በለይቶ ማቆያ ያሉ፣ 11 ሰዎች ከሶማሌ ክልል የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸውና ለይቶ ማቆያ ያሉ ሲሆን፤ 4 ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው ድንበር ተሻጋሪ የመኪና አሽከርካሪዎች ናቸው።
በዚህም መሰረት ዛሬ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች 34ቱ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 4 በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 8 ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክም ሆነ በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር የታወቀ ግንኙነት የሌላቸው መሆናቸውን ዶክተር ሊያ በፌስቡክ ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።
በሌላ በኩል በተጓዳኝ ህመም ምክንያት በጽኑ ህክምና ላይ የነበረች እና ትላንት የኮሮና ቫይረስ በምርመራ የተገኘባት የ32 ዓመት የአዲስ አበባ ነዋሪ ህይወቷ በማለፉ በኢትዮጵያ አጠቃላይ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 6 ደርሷል።
በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ ሰዎች 526 ናቸው።
ተጨማሪ 8 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን በአጠቃላይ 167 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
አንድ ሰው በጽኑ ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገለት መሆኑም ታውቋል።
የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መጨመርን ከግንዛቤ በማስገባት ህብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን አዘውትሮ እንዲተገብር በማሳሰብ፤ ህይወታቸው ባለፈው ግለሰብ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
እስካሁን አጠቃላይ 87, 264 የላቦራቶሪ ምርመራ መከናወኑን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል።