ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ለሚገኙ ለይቶ ማቆያ ማዕከላት 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

መተማ፣ ግንቦት 18/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ የለይቶ ማቆያ ማዕከላት የተስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

ዞኑ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በመጋለጡ ሌሎች የክልሉና የፌደራል መንግሥት ተቋማት ተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ የዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ጥሪ አቅርቧል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊና የክልሉ ግብረ ኃይል ፀሐፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ድጋፉን ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ዞኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ከሱዳን በመመለስ ወደ ለይቶ ማቆያው ይገባሉ።

ከስደት የሚመለሱት ዜጎችም ከዋና ዋና መግቢያ በሮች ባሻገር በጫካ ውስጥ አልፈው ለመግባት የሚሞክሩበት አጋጣሚ በመኖሩ የኮሮና መከላከል ሥራውን ፈታኝና በርካታ ወጪ የሚጠይቅ እንዲሆን አድርጎታል።

ከስደት ተመላሾችን በመያዝ ወደ ለይቶ ማቆያ በማስገባት ጤንነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ ባይሰራ ኖሮ ተመላሾቹ ወደ ሁሉም ክልሎች የሚሄዱ በመሆናቸው የቫይረሱን ሥርጭት የከፋ ያደርገው ነበር ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም የክልሉ ጤና ቢሮ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን  ጠቁመው  ድጋፉም በለይቶ ማቆያ ቦታዎች የሚስተዋለውን  የቁሳቁስና ሌሎች  ክፍተቶችን ለመሙላት የሚውል ነው።

በቀጣይም የባለሙያ ሥልጠናና የአበል ክፍያ ለመሸፈን መወሰኑን ጠቁመው የመተማ ሆስፒታል ምርመራ እንዲጀምር ለማድረግ የኦክስጅን፣ ሲሊንደሮችና አራት መካኒካል ቬንትሌተሮች ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ከችግሩ ስፋት አንጻር የክልሉና የፌደራል መንግሥታት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ቫይረሱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እንዳይስፋፋ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን የማኅበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊና የግብረ ኃይሉ ፀሐፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ በበኩላቸው በዞኑ በሚገኙ ስድስት ለይቶ ማቆያ ማዕከላት  700 የሚጠጉ  ዜጎች የኮሮና ቫይረስ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል።

"በማቆያ ለሚገኙ ዜጎችም የመኝታ፣ የምግብ፣ የንጽሕና መጠበቂያና ለባለሙያዎች የሚሆን የመከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ማጋጠሙን ጠቁመው ቢሮው ያደረገው ድጋፍ ችግሩን ለማቃለል የሚያግዝ ነው" ብለዋል።

በርካታ ዜጎች አሁንም ከሱዳን ወደ ዞኑ በጫካ እየገቡ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየሄዱ በመሆኑ በሕገወጥ መንገድ የሚገቡትን ለመቆጣጠር በዞኑ ካሉ የፀጥታ አካላት ተጨማሪ ኃይል እንዲመደብላቸው ጠይቀዋል።

እስካሁን ከሰባት ሺህ በላይ ዜጎች የሙቀት ልኬት የተደረገላቸው ሲሆን ከአንድ  ሺህ  200  በላይ የሚሆኑ ዜጎች ደግሞ በለይቶ ማቆያ ምርመራ ተደርጎላቸዋል።


በቢሮ ኃላፊው የተመራው ቡድን በመተማ ዮሐንስ፣ በኮኪትና በገንዳውኃ ከተማ የሚገኙ የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ማዕከላትን ተዘዋውረው መጎብኘታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም