ቀጥታ፡

አራተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር በአዲስ አበባ ተጀምሯል

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 አራተኛው ዙር ብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድር ትናንት በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል። በውድድሩ ላይ በሀለቱም ጾታዎች ከስድስት ክለቦች የተወጣጡ 70 ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ነው። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ፌደራል ፖሊስ፣ፌደራል ማረሚያ፣ማራቶን፣ድሬዳዋ ከነማና ልደታ ክፍለ ከተማ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ናቸው። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብደቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ። ተተኪ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ማፍራት የውድድሩ ዓላማ እንደሆነ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው ዓመት የብሔራዊ የክለቦች ቦክስ ውድድሮች በአዲስ አበባ፣ ሆሳዕና እና ጎንደር ከተሞች ማካሄዱ ይታወሳል።  በአዲስ አበባ የሚካሄደው ውድድር የዘንድሮ ዓመት የክለቦች መዝጊያ ውድድር እንደሆነና በአጠቃላይ በአራቱም ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ተደምሮ የ2010 ዓ.ም የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል። ትናንት በተጀመረው ውድድር ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች በዚህ ዓመት ከተካሄዱ ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች አንጻር ሲታይ አነስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል። ከዚህ በፊት በተካሄዱት ውድድሮች 10 ቡድኖች ይሳተፉ እንደነበር አስታውሰው በዚህ ምክንያት የሚካሄዱ ጨዋታዎች ቁጥር በማነሳቸው ከነገ በስቲያ ይጠናቃቀል የተባለው ውድድር ነገ እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም