ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 ዘጠኝ ቡድኖች የሚሳተፉበት የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። ነገ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም መከላከያ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ ቡታጅራ ከተማ በሜዳው ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተመሳሳይ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ይጫወታሉ። ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዲየም ፌዴራል ማረሚያ ከመቐለ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከፌዴራል ፖሊስ ከረፋዱ 5 ሰአት ላይ የሚጫወቱ ይሆናል። የዓመቱ ሊግ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በ28 ነጥብ ሲመራ፣ መቐለ ከተማ በ21 ነጥብ ሁለተኛ እንዲሁም ፌዴራል ፖሊስ በ20 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። በሂሳባዊ ስሌት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ መቐለ ከተማ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማና ፌዴራል ፖሊስ የሊጉ አሸናፊ የመሆን እድል አላቸው። ቡታጅራ ከተማ 2 ነጥብ ብቻ በመያዝ የሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ባለፈው ዓመት የተጀመረ ውድድር ሲሆን መከላከያ የመጀመሪያ የዋንጫ ባለቤት መሆኑ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም