በአዳማ ከተማ በአሰቃቂ የነብስ ግድያ ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት ተቀጣ

114

አዳማ /ኢዜአ/ ግንቦት 17/2012 በአዳማ ከተማ በአሰቃቂ የነብስ ግድያ ወንጀል የተከሰሰ ግለሰብ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት መቀጣቱን የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ።

የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ሰቦና ጉተማ  እንደገለጹት ኢ-ሰብዓዊ የሆነና ጭካኔ በተሞላበት አሰቃቂ ሁኔታ በነብስ ግድያ ወንጀል ተከሶ በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተቀጣው ብርሃን ዓለሙ የተባለ ግለሰብ ነው ።

ተከሳሹ መስከረም 17 ቀን 2012 ዓም እኩለ ሌሊት ላይ  በአንድ ቤት ውስጥ ተከራይተው አብሮት የሚኖር ሰው 1 ሺህ 600 ብር ወስዶ አልመለሰልኝም በማለት የግድያ ወንጀሉን እንደፈፀመበት ዳኛው ተናግረዋል።

ማቹና ገዳዩ በቁሳቁስ ልዋጭ ሥራ የተሰማሩ ሲሆን በአዳማ ከተማ ገዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዓለም ሆቴል አካባቢ ተከራይተው አብረው ይኖሩ እንደነበርም በክስ መዝገቡ ገልጿል።

ግለሰቡ የገዛ ጓደኛውን አብሮ በሚኖሩበት ቤት ውስጥ በመጥረቢያ ጭንቅላቱን በመምታት እንደገደለውም ዳኛው አብራርተዋል ።

በአካባቢው ሲጫወቱ የነበሩ ልጆች ተቆርጦ የተጣለውን የሰው አካል በማየት ለፖሊስ ባደረሱት ጥቆማ መሰረት በተደረገው ክትትል በተከራዩት ቤት ውስጥ ሶስት ቦታ ተቆርጦ በማዳበሪያ የተቀመጠውን የሟች አካል እንደተገኘና ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ሚኒሊክ ሆስፒታል መላኩን የክስ ማስረጃው ያመላክታል ።

ድርጊት ፈፃሚው ከአካባቢው ተሰውሮ የነበረ ቢሆንም በፖሊስ ጥብቅ ክትትል ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓም በአርሲ ዞን አሰላ ከተማ ከተሸሸገበት ቦታ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል ።

ግለሰቡ ጥፋቱን መፈፀሙን በሰነድና በሰው ማስረጃ ከመረጋገጡም ባለፈ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ግንቦት ፍርድ ቤቱ ግንቦት 17 ቀን 2012 ዓም በዋለው ችሎት በእድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተወስኖበታል ብለዋል።

በተመሳሳይ ሁኔታ በአዳማ ከተማ ቢቃ ቀበሌ አዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል ገብቶ ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በ13 ዓመት ፅኑ እስራት መቀጣቱን ፍርድ ቤቱ አያይዞ ገልጿል።

አሊ ናስር የተባለ ተከሳሽ የካቲት 10 ቀን 2012 ዓም 546 ሺህ 685 ብር ግምት ያላቸው ቴሌቪዥኖችንና የተለያዩ ንብረቶችን በመዝረፉ ነው የተቀጣው ተብሏል።

ግለሰቡ ጨለማን ተገን አድርጎ ወደተለያዩ ሆቴሎች በመግባት የተለያዩ ንብረቶችን መዝረፉን በምርመራ መረጋገጡን የጠቀሱት ዳኛው የአንገት ሃብል፣ የጆሮ ጌጥ፣ የእጅ ብራስሌት፣ ሞባይል፣ ላፕ ቶፕና ቴሌቪዥኖችን ከአዳማ፣ ሞጆና ቢሾፍቱ ከተሞች መስረቁንም በተደረገው ምርመራ መጣራቱን ገልጸዋል።

ፖሊስ ወንጀለኛውን ጨምሮ ንብረቱን የገዙት 18 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር በማዋል ለፍርድ ቤት በማቅረቡ ፍርድ ቤቱ በዛሬው የችሎት ውሎው ዋናው ተከሳሽ ዓሊ ናስር በ13 ዓመት ፅኑ እስራትና ቀሪዎቹ ተባባሪዎች ደግሞ እንደየጥፋታቸው መጠን በገንዘብ እንዲቀጡ መወሰኑን ዳኛው ኢዜአ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም