የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ውድድር ለ20 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ

አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 በርዋንዳ ለሚካሄደው ሶስተኛው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለ20 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ። የሴካፋ ውድድር ከሐምሌ 12 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ለሴካፋው ውድድር የቅድመ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) ውድድሩን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገውን ወጪ በተቀመጠለት ጊዜ ለአዘጋጇ ሩዋንዳ ባለመላኩ ውድድሩ በተደጋጋሚ  ሲራዘም ቆይቷል። በዚህም ምክንያት የዘንድሮው ውድድር የመካሄድ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኖ ቆይቶ ነበር። በአሰልጣኝ ሰላም ዘርአይ የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን 'ሉሲዎች' ለውድድሩ እንዲረዳው ከሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ አበባ ላይ ዝግጅት ሲያደርግ ቢቆይም የውድደሩ መካሄድ በማጠራጠሩ ቡድኑ ዝግጅቱን አቁሞ ነበር። በአሁኑ ሰአት ግን ሴካፋ ለርዋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  የሚያስፈልገውን በጀት በመልቀቁ ምክንያት ውድድሩ የሚካሄድ ይሆናል። በውድድሩ ላይ አዘጋጇ ርዋንዳን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ ይሳተፋሉ። የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ የክለቦች ማህበራት ምክር ቤት (ሴካፋ) የተለያዩ የአፍሪካ የብሔራዊ ቡድንና የክለቦች ውድድር ለማስተናገድ የፋይናንስ ችግር በስፋት ሲገጥመው ይስተዋላል። ከሁለት ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውድድሩን ካስተናገደች በኋላ የሴካፋ የሴቶች እግር ኳስ ውድድር በበጀት ማጣት ምክንያት መዘግየቱ ይታወሳል። የሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ1986 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዛንዚባር ውድድሩን ያሸነፈች ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር ታንዛንያ አሸናፊ መሆኗ ይታወሳል። በኡጋንዳ በተካሄደው ውድድር የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎች አዘጋጇ ኡጋንዳን አራት ለአንድ በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁበት ከፍተኛ ያስመዘገቡት ውጤታቸው ነው። ለሴካፋ ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ጥሪ የተደረገላቸው 20 ተጫዋቾች ዝርዝር ከዚህ እንደሚከተለው ቀርቧል። ከመከላከያ ስፖርት ክለብ እመቤት አዲሱ ከሀዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ምርቃት ፈለቀ ልደት ቶሎ ከደደቢት እግር ኳስ ክለብ ገነት አክሊሉ መስከረም ኮንካ ሠናይት ቦጋለ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ትዕግስት ዘውዴ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስፖርት ክለብ ንግስት መዓዛ ታሪኳ ዴቢኮ ዙሌይካ ጁሀድ ሕይወት ደንጊሶ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ መሠሉ አበራ ብዙአየሁ ታደሠ ቤዛዊት ተስፋዬ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ስፖርት ክለብ ቤቴልሔም ከፍያለው አለምነሽ ደመቀ ከኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ አረጋሽ ካልሳ ከጥረት ኮርፖሬሽን ምስር ኢብራሂም አሣቤ ሞኢሶ ታሪኳ በርገና ከአዳማ ከተማ ስፖርት ክለብ ሴናፍ ዋቁማ
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም