ቀጥታ፡

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ሰሜን ሸዋ ነዋሪዎች ገለጹ

ፍቼ ፣ግንቦት 17/2ዐ12/ኢዜአ/ የኮሮና ቫይረስ ከመከላከሉ በተጓዳኝ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የዞኑ ህዝብ ለግድቡ ግንባታ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ  ድጋፍ ማድረጉ ተመልክቷል።

ከነዋሪዎች መካከል የደብረ ሊባኖስ ገዳም አስተዳዳሪ ቄስ ዋስይሁን አሰፋ ወረርሽኙን በመከላከል ለሀገራዊ አንድነትና መተባበር ተምሳሌት የሆነው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ዋጋ መክፈል ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው ይካሄዱ የነበሩ የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና ግድቡ ለፍፃሜ እንዲበቃ የድርሻቸውን ለመወጣት እንደተዘጋጁም ገልጸዋል፡፡ 

የሰሜን ሸዋ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስተባባሪ ሀጂ ሙፍቲ መሀመድ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ለግድቡ ግንባታ የአካባቢው ሙስሊም ህብረተሰብ በሁለት ዙር ከወለድ ነፃ የአንድ መቶ ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሁኔታዎች እየተመቻቸ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 

የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ የእድገትና የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ድጋፋቸው እስከ ፍፃሜ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ 

ወቅታዊውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከመከላከሉ በተጓዳኝ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ እንዲቀጥል የበኩላቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ይርገዱ አያሌው ናቸው።

በግላቸውም በሁለት ዙር ከሶስት ሺህ ብር በላይ ቦንድ ገዝተው ግድቡን መደገፋቸውን አመልክተዋል፡፡ 

በፍቼ ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ ሙራድ ሙሀመድ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚነት መብት መሆኑን ጠቁመው "የግብፅ ኢ-ፍትሃዊ የተጠቃሚነት ጥያቄ ግን የሚወገዝ ነው" ብለዋል፡፡ 

በእሳቸው በኩል ያላቸውን ጉልበትና ገንዘብ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ተናግረዋል። 

በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅቶ በብረታ ብረት ስራ የተሰማራው ወጣት ደጀኔ አስፋው በበኩሉ ቀደም ባሉት ዓመታት ከገዛው የአንድ ሺህ ብር ቦንድ በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የድጋፍ ጥሪ ከቀረበ የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት መፈለጉን ገልጿል፡፡ 

ኮሮናን  ለመከላከል ከሚያደርጉት ጥረት ጎን  የግድቡ ግንባታ እንኪጠናቀቅም  በገንዘብ ፣እውቀትና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጐትና ተነሳሽነት እንዳላቸው  የፍቼ ከተማ የሀገር ሽማግሌ አቶ ታሪኩ ለገሰ ተናግረዋል።

መምህር በነበሩ ደምሴ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አሰረድተዋል።

ከዚህ ቀደም ከገዙት የ2ሺህ ብር ቦንድ በተጨማሪ ባላቸው አቅም ሁሉ ለግድቡ ግንባታ መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የዞኑ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ አቶ ቅናጢ ጫላ እንዳመለከቱት  የዞኑ ህዝብ ባለፉት ሁለት ዙሮች በተደረገው ንቅናቄ ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅትም  የመንግስት ሰራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፋቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማስተባበርና የማነቃቃት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም