ኪነ-ጥበብ ለሰላምና ልማት መጠናከር ሚናውን እንዲጫወት ሙያተኛው ራሱን ማዘጋጀት አለበት ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ኪነ-ጥበብ ለሰላምና ልማት መጠናከር ሚናውን እንዲጫወት ሙያተኛው ራሱን ማዘጋጀት አለበት ተባለ
አዲስ አበባ ሰኔ 29/2010 የኪነ-ጥበብ ዘርፉ ለአገራዊ ሰላምና ልማት መጠናከር የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ሙያተኛው በአዲስ መንፈስና ትጋት መስራት እንዳለበት ተገለፀ። ይህ የተገለፀው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ባዘጋጀው በሙዚቃ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ፋይዳው ላይ በማተኮር በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ ነው። በመድረኩ ላይ ሙዚቃ ከማዝናናት ባሻገር በሰው ልጆች መካከል መቀራረብን በመፍጠር ምጣኔ ኃብታዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ስነ-ልቦናዊና ሰብዓዊ እድገትን ለማምጣት የጎላ ሚና እንደሚጫዎት የሚታወቅ ቢሆንም ይህንን ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ተብሏል። የሙዚቃው ኢንዱስትሪ አሁንም ድረስ በየጊዜው ለሚመጡት ስርዓቶች መገልገያ ከመሆን ባለመውጣቱ ከማደግ ይልቅ እየተዳከመ እንደመጣ ተነግሯል። ''ከዚህም ሌላ በሙያው የተሰማሩ አንዳንዶች ለጊዜያዊ የገንዘብ ጥቅም ሲሉ ከፈጠራ ይልቅ በዜማ ኩረጃ ተጠምደው ይታያሉ'' ሲሉም የመድረኩ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። "ባላገሩ አይዶል" በተሰኘው የሙዚቃና ውዝዋዜ ውድድር ዝግጅቱ የሚታወቀው አርቲስት አብርሃም ወልዴ በሰጠው አስተያየት ሙያው ነጻነትን የሚሻ፣ ፍቅርንና እውነትን የሚሰብክ መሆን ሲገባው በየጊዜው በሚፈጠሩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በመጠለፉ ዘርፉ በሚፈለገው መጠን ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ተናግሯል። ዘርፉ አገራዊ ፋይዳ ያለው ተግባር እንዲከውን "እንደመንግስት ይቅርታ ጠይቀን፤ ከራሳችን ጋር ታርቀን ወደ ሙያው እንድንመለስ ያስፈልጋል፤ ይህ ካልሆነ ግን ኢንዱስትሪው አደጋ ላይ ይወድቃል" ብሏል። የሌሎች ሥራዎችን በመኮረጅ አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለመሰብሰብ በሚጥሩትና ለዘረፉ እድገትም እንቅፋት እየሆኑ ባሉ አካላት ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ እንዲጠናከር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑንም አርቲስት አብርሃም አመልክቷል። በመሆኑም መንግስት የኪነ-ጥበብ ሙያ የሚሻውን ነጻነትና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ረገድ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲጫወት ተሳታፊዎቹ ጠይቀዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ለመጀመሪያ ጊዜ በአገሪቱ የሙዚቃ ሙያን ለማገዝ የተዘጋጁ መሪ በመሆናቸው ወደፊት ዘርፉ ያለበትን ችግር ለማቃለል የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት እንዳለው አርቲስት አብረሃም ገልጿል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፎክሎር ዲፓርትመት ተማሪ መስፍን መሰለ በሰጠው አስተያየት ብሔራዊ አንድነትንና አገራዊ ፍቅርን የሚያጠናክሩ የጥበብ ሥራዎች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ እንዳልሆነ ተናግሯል። በአገሪቱ ስነ-ምግባርንና ሙያዊ ብቃትን የሚያረጋግጡ የሙዚቃ ጥበብ ሙያተኞችን ለመፍጠር ዘረፉ ተገቢ በሆነ መጠን በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ ሊካተት ይገባል ተብሏል። ባህልና ቱሪዝም መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ከዘርፉ ሙያተኞች ጋር ተቀራርበው በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታም ሊመቻች እንደሚገባው የመድረኩ ተሳታፊዎች አሳስበዋል። ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ዮሐንስ ብርሃኑ በበኩሉ በሙዚቃና ማህበራዊ ፋይዳው ዙሪያ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች መለየትና መፍትሄ መዘየድ እንደሚገባ ጠቅሷል።