ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ልብስ ስፌት ማህበራት ፌዴሬሽን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያግዝ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ልብስ ስፌት ማህበራት ፌዴሬሽን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ግምቱ 360 ሺህ ብር የሆነ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ፌዴሬሽኑ በድጋፍ ያቀረበው ደረቅና ፈሳሽ ሳሙና፣ አልኮል እና ሳኒታይዘር በአዲስ አበባና አካባቢዋ ለሚገኙ 40 የፌደሬሽኑ አባል ማህበራት ነው፡፡ በማህበራቱ ስር ከ54 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንደታቀፉም ተጠቁሟል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አንገሶም ገብረስላሴ ''አምራች ድርጅት የሚኖረው ሰራተኛ ሲኖር በመሆኑ ሰራተኛው ራሱን ከወረርሽኙ ለመጠበቅ እንዲችል ድጋፍ አድርገናል'' ብለዋል፡፡

ሰራተኛው በስራም ሆነ ከስራ ውጭ በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የቅድመ መከላከል መመሪያና ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

የስራ ባህሪው የሰውን መቀራረብ የሚጠይቅባቸው ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሰራተኞች ሳይዘናጉ ጥንቃቄ በማድረግ ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣ ድርጅታቸውንና አገራቸውን መታደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ልብስ ስፌት ማህበራት ፌደሬሽን ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረገው ድጋፍ ዓረአያነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በጨርቃ ጨርቅ አምራች ሴክተሩ ውስጥ ሰራተኛ የሚበዛበት፣ ከፍተኛ ንክኪና የስራ ቅብብሎሽ ስላለ ሰራተኛው ጥንቃቄ እንዲያደርግና እንዳይዘናጋ የማህበራት መሪዎች በየጊዜው ክትትል እንዲያደርጉ አስገንዝበዋል።

የኤም ኤን ኤስ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ተመስገን ሰጠኝ ወረርሽኙ በአንዱ ሰራተኛ ላይ ቢከሰት አደጋው ሊከፋ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በመሆኑም የቅድመ መከላከል ስራ መጠናከር ስለሚገባው የተደረገው ድጋፍ ለዚህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮ-ሌዘር ኢንዱስትሪ የጥቁር ዓባይ የመሰረታዊ ሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበበ መንግስቴ፤ ወረርሽኙን ለመከላከል ድርጅቱ የቀንና የሌሊት ፈረቃ በማውጣት የሰራተኛ መተፋፈግና ንክኪን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሰራተኛ ማህበራት መሪዎች ድርጅቶቻቸው በመንግስትና በጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ የቅድመ ጥንቃቄ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ሰራተኛው ጥንቃቄ እያደረገ እንዲሰራ መደረጉንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ልብስ ስፌት ማህበራት በፌዴሬሽን በአገር አቀፍ ደረጃ 118 ማህበራት አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም