ለጎንደር ከተማ 50 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለጎንደር ከተማ 50 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ድጋፍ ተደረገ
ጎንደር፣ ግንቦት 17/2012 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተካሄደ ላለው ተግባር የሚውሉ 50 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች በድጋፍ ማግኘቱን የከተማው ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።
ድጋፉን የሰጡት በእስራኤል የሚኖሩ የጎንደርና የአካባቢው ተወላጆች ናቸው።
የግብረ ኃይሉ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ፀሐፊ ወይዘሮ የሻረግ አብድራህማን ለኢዜአ እንደተናገሩት መሳሪያዎቹ ቤት ለቤት ለሚካሄደው የልየታ ስራና በከተማው ለሚገኙ የህክምና ተቋማት የሚሰጥ ይሆናል።
ከ750 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው እነዚህ መሳሪዎች ኮሮናን በተሻለ አቅም ለመከላከል ያግዛል ብለዋል።
በተመሳሳይ የጎንደር ህብረት 300 ሺህ ብር ግምት ያላቸውን 302 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና 600 ሊትር የምግብ ዘይት በድጋፍ መስጠቱንም ወይዘሮ የሻረግ ጨምረው ገልጸዋል።
በከተማው በኮሮና ምክንያት ለተቸገሩ ከ65 ሺህ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ሃብት በማሰባሰብ ለመደገፍ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት 9 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ፣ ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በማሰባሰብ ለተጠቃሚዎች እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የከተማው ህብረተሰብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ክልከላዎች በማክበር እራሱን ከበሽታው እንዲጠበቅ ግብረ ሃይሉ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡