በኢትዮጵያ ተጨማሪ 73 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

99

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 17/2012( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባለፉት 24 ሰዓት በተደረገ 2844 የላቦራቶሪ ምርመራ ተጨማሪ 73 ሰዎች ኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።

በዚህም እስካሁን በኢትዮጵያ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 655 ደርሷል።

ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው 49 ወንዶች እና 24 ሴቶች ሲሆኑ 67ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

ዶክተር ሊያ እንደገለፁት ዛሬ ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች 27ቱ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ አላቸው፡፡

በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከ6 እስከ 75 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 56 ሰዎች ከአዲስ አበባ(ሶስት ሰዎች ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው ሲሆኑ 12 ሰዎች የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው እንዲሁም 31 ሰዎች በሽታ ካላቸው ጋር የታወቀ ንክኪ ያልነበራቸው እንዲሁም የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያልነበራቸው) ናቸው፡፡

ስምንት ሰዎች ከሶማሌ ክልል ጂግጂጋ ለይቶ ማቆያ ሲሆን የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው፤ አራት ከትግራይ ክልል ለይቶ ማቆያ የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው እንዲሁም ሁለት ሰዎች ከአማራ ክልል ሲሆን በሽታው ካለው ሰው ጋር የታወቀ ንክኪ ያላቸው ናቸው፡፡

እንዲሁም ሶስት የውጭ ሀገር ጉዞ ታሪክ ያላቸው የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

ተጨማሪ 7 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን አጠቃላይ 159 ደርሷል፡፡ አንድ ሰው በጽኑ ህክምና ነው።

በአጠቃላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው በለይቶ ህክምና ውስጥ ያሉ ሰዎች 489 መሆናቸውንም ዶክተር ሊያ ገልጸዋል።

እስካሁን በኢትዮጵያ አጠቃላይ 83 ሺህ 854 የላቦራቶሪ ምርመራ ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም