ቀጥታ፡

ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ 70 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከጎዳና እንዲነሱ ተደርጓል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 17/2012 ዓ.ም ( ኢዜአ)  በጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩ 70 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ወደ ማዕከላት እንዲገቡና ከቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉን የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።


ሚኒስቴሩ ለኢዜአ እንደገለጸው ከ67 ሺህ በላይ የሚሆኑት ዜጎች ከጎዳና ተነስተው ወደ ማዕከላትና ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል። 

የልማታዊ ሴፍቲኔት አስተባባሪው አቶ ተስፋዬ ሽፈራው እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ማህበራዊ ጫና ለመቀነስ በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።  

ከዚህም መካከል ተጋላጭ የኀብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት የግንዛቤ ማስጨበጫ መስጠትና ድጋፍ ማድረግን ጠቅሰዋል። 

ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎች ከተጋላጮች መካከል በመሆናቸው ከቫይረሱ ለመጠበቅ ሲባል ከማህበራትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ስራው መከናወኑን ተናግረዋል።

በእስካሁን ሂደት በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በአማራ ክልሎች ከ42 ሺህ 600 በላይ ዜጎች ከጎዳና ላይ ተነስተው ወደ ተለያዩ ማዕከላት መግባታቸውን አብራርተዋል። 

ከ23 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማቀላቀል ሥራ ተሰርቷል፤ 2 ሺህ ህፃናትም በልማታዊ ሴፍቲኔት በኩል ተነስተዋል ነው ያሉት።

ቀደም ሲል በ11 ዋናዋና ከተሞች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 88 ሺህ 690 ሰዎች ኑሯቸውን ጎዳና ላይ እንዳደረጉ መታወቁን አንስተው፣ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ጎዳና ላይ ያሉ ዜጎችን ቁጥር ከፍተኛነት  እንደሚያሳይ አስረድተዋል። 

በቀጣይም ከ5 ሺህ በላይ በጎዳና ላይ ያሉ ዜጎችን ለማንሳት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ኀብረተሰቡ ባለው አቅም ሁሉ ተጋላጭ የኀብረተሰብ ክፍሎችን ከቫይረሱ ለመከላከል እንዲተጋም አቶ ተስፋዬ ጥሪ አቅርበዋል። 

በዚህ ተግባር መሳተፍ ለሚሹ አካላትም ጥሪ አቅርበዋል።

ከሚኒስቴሩ የልማት አጋሮች አንዱ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን ከአዲስ አበባና ሐዋሳ ከተሞች ጎዳና ላይ የነበሩ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎችን በማዕከሉ አስጠልሏል። 

የሐዋሳ ምክትል ከንቲባ ጥራቱ በየነ እንደገለጹትም ከተማ አስተዳደሩ ግብረ-ኃይል በማቋቋም ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ከወረርሽኙ ለመከላከል እየሰራ ነው። 

ይህን ተግባር ለማገዝ እንዲረዳ 11 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብና 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት በአይነት የተሰባሰበ ሃብት መኖሩንም ተናግረዋል። 

ከግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በተጨማሪ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተጓዦችን ሙቀት የመለካት ስራው ይከናወናል።

ከበሽታው መከላከያ መንገዶች አንዱ በቤት ውስጥ መቆየት በመሆኑ ይህን ማድረግ የማይችሉ ህይወታቸውን በጎዳና የሚመሩ ዜጎችን ለመለየት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷልም ብለዋል። 

በጥናቱ 1 ሺህ 500 ዜጎች መኖራቸው የተረጋገጠ ሲሆን 1 ሺህ የሚጠጉት ከጎዳና ተነስተው በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወርሃዊ ቀለብ እየተደገፉ በኤልሻዳይ ማዕከል እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ ህይወታቸውን በጎዳና ያደረጉ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ ለማንሳት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ምክትል ከንቲባው አክለዋል።  

ሌሎች ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ለማድረግ ከማህበረሰቡ ጋር እንደሚሰራ ተናግረው፤ ኀብረተሰቡ በዚህ በኩል ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል።

የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን መሥራች አቶ የማነ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ ማህበራቸው በአዲስ አበባና ሐዋሳ ከተሞች ጎዳናዎች ላይ ለነበሩ ከ2 ሺህ በላይ ሰዎች መጠለያ መሆኑን ገልፀዋል። 

በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የማህበሩ ማዕከላት 30 ሺህ ሰዎችን ማስጠለል እንደሚችሉ ገልፀው፤ ቀሪዎቹን ዜጎች ከጎዳና ለማንሳት ርብርብ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም