ቀጥታ፡

በትግራይ ቫይረሱን ለመከላከል 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

መቐለ፣ ግንቦት 15 /2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በትግራይ የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ከባለሃብቶችና ከአንድ የንግድ ድርጅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ ዛሬ መረከቡን የክልሉ ግብረ ኃይል ገለፀ ።

 የግብረ ኃይሉ ኣባል የሆነው የክልሉ ጤና ቢሮ ዛሬ ከተረከባቸው የቁሳቁሶች ድጋፍ መካከል በመቐለ ከሚገኙ ስምንት ባለሃብቶች የተሰጠው 950 ሺህ ብር ገምት ያላቸው የተለያዩ መድሃኒቶች፣ የንፅህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮች፣ ብርድልብሶች፣ አንሶላዎች ፣የስንዴ ዱቄትና የተለያዩ የምግብ አይነቶች ይገኙባቸዋል።

ባለሃብቶቹ በክልሉ የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት አማካኝነት ያስረከቡት ሲሆን ድጋፋቸው ቀጣይነት እንደሚኖረው በርክክቡ ስነ ስርዓት ላይ ተገልጿል።

የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ሼር ካምፓኒ በበኩሉ 700 ሺህ ብር ዋጋ የሚያወጣ ሳኒታይዘርና ለስላሳ መጠጦች ለግብረ ሃይሉ አስረክቧል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊና የሎጂስቲክስና መድሃኒት አቅርቦት ንኡስ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሐጎስ ጎዲፋይ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ ለተደረገው ድጋፍ በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አመስግነዋል።

 የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የባለሃብቶች ተሳትፎ እያደገ መምጣቱንም ዶክተር ሐጎስ ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሸናፊ ሃይሉ በበኩላቸው ድጋፉ ባለሃብቱ መንግስት ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎን መሰለፉን ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

የተደረገው ድጋፍ ሌሎች ባለሃብቶችና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳ መሆኑንም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።

በመቐለ የኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ሼር ካምፓኒ ወኪል አቶ የማነ ገብረሊባኖስ እንዳሉት ደግሞ ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የተበረከተው ድጋፍ ለወደፊቱም ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም