ቀጥታ፡

ኢድ አልፈጥርን ምክንያት በማድረግ ለ520 ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

ደሴ፣ ግንቦት 15/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በደሴና ገርባ ከተሞች የኢድ አል ፈጥርን በዓል ምክንያት በማድረግ ለ520 አቅመ ደካሞች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል  ወይዘሮ መዓዛ ኃይለጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት አቅመ ደካሞች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህ ወቅት ከ36 ሺህ በላይ አረጋውያን፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና ህጻናት አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ተለይተዋል።

እስካሁንም ወጣቶች፣ ባለሃብቶችና ሌሎች በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ከ4 ሺህ ለሚበልጡ አቅመ ደካሞች ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ከ2 ሺህ 500 የሚበልጡ የጎዳና ተዳዳሪዎችንም ከወሎ ዩንቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በመውሰድ ከቤተሰብ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፡፡

በዛሬው እለትም በደሴ ከተማ አስተዳደርና በቃሉ ወረዳ ገርባ ከተሞች የሚገኙ 520 አቅመ ደካሞች የኢድ አል ፈጥርን በዓል ምክንያት ማድረግ 490 ሺህ ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ ተደርጓል።

በደሴ ከተማ የተሰጠው ድጋፍ "በአርሂቡ" ለሰላምና ልማት መረዳጃ ማህበር የተሰጠ ሲሆን  በገርባ ከተማ የቀረበው ድጋፍ ደግሞ በሌሎች ወጣቶች አስተባባሪነት የተሰበሰበ ነው ።

የ"አርሂቡ" ለሰላምና ለልማት መረዳጃ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ጣፈጠ ተስፋዬ እንደተናገረው ማህበሩ ከተመሰረተ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ ለሰላምና ለልማት የድርሻውን እያበረከተ ነው፡፡

በዛሬው እለትም የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸውን ሰዎች በመለየት የዳቦ የዱቄት፣ ሩዝ፣ ማካሮኒና ዘይት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጾ እስካሁን 500 የሚጠጉ ዜጎች መደገፋቸውን አስታውሷል፡፡

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አቶ እሸቱ ሁሴን በሰጡት አስተያየት በቀን አስራ ሶስት ቤተሰብ ያስተዳድሩ እንደነበረ ገልጸው አሁን በኮሮና ምክንያት ስራ በመቆሙ ለችግር ተጋልጬ ነበር ብለዋል፡፡

በዛሬው እለትም 31 ኪሎ ግራም ዱቄት፣ ሩዝ፣ ማኮሮኒና 3 ሊትር ዘይት ከንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ጋር ድጋፍ  እንዳገኙ ጠቅሰው ይህም ወቅታዊ ችግሩን ለመቋቋም ያግዛል ብለዋል።

የተደረገላቸው ድጋፍ የኢድ አልፈጥር በዓልን አቅም በፈቀደ መጠን ለማክበር ያግዘናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጤ አበጋዝ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም