ቀጥታ፡

በአዋጁ አተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ስጋት አሳድረውብናል -የምስራቅ ወለጋ ነዋሪዎች

ነቀምቴ ፣ ግንቦት 15/2012 (ኢዜአ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በትራንስፖርት ዘርፍ ያስቀመጣቸው ክልከላዎች አተገባበር ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ለቫይረሱ ሊያጋልጡን ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ ።

አስተያየት ከሰጡት መካከል የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ አቶ ኤቢሣ ጉያሣ እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግሥት የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚፈለገው መጠን ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም ብለዋል ።

በመናኽሪያዎች አካባቢ ተሳፋሪው እርስ በርስ በመገፋፋት አካላዊ ንክኪ እንደሚታይበትና የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ትርፍ በመጫን አዋጁ ካስቀመጠው ታሪፍ በላይ በማስከፈል ችግር እየፈጠሩ ናቸው ሲሉ ትዝብታቸውን ተናግረዋል ።

የዲጋ ከተማ ነዋሪ አቶ መኮንን ጎላሣ በበኩላቸው በተለይም የሕዝብ ማመላለሻ ሚኒባሶችና ሞተር ብስክሌቶች ትርፍ እንደሚጭኑና ከታሪፍ በላይ እንደሚያስከፍሉ ተናግረዋል፡፡

የጉቶ ጊዳ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ እንዳሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ለማድረግ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር  የላላ በመሆኑ አሽከርካሪዎች ትርፍ በመጫን ለቫይረሱ  ተጋላጭ የሚያደርግ አሰራር እንደሚከተሉ ጠቁመዋል ።

ቫይረሱ ተስፋፍቶ ህዝቡ ለችግር ከሚጋለጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል ፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዓለማየሁ እምሩ ስለ ሁኔታው ተጠይቀው በቁጥጥሩ ሒደት ክፍተቶች መኖራቸውን በማመን ከዞኑ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው የእርምት እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስረድተዋል ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ደረጀ አበራ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር መንግሥት ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመተግበር ጥረቶች ተደርገዋል ።

አልፎ አልፎ መዘናጋቶች መኖራቸውን ገልፀው የዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ ሲባል አዋጁን በሚተላለፉ አካላት ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ አርምጃ ለመውሰድ ተገቢው ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል ።

በተለይ ደግሞ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ አቅጣጫ መቀመጡን የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም