ቀጥታ፡

በትግራይ የ800 ጥንዶች ሰርግና ድግሶች እንዲራዘሙ ተደረገ

አክሱም ፣ ግንቦት 15/2012 ዓ.ም (ኢዜአ) በትግራይ ማዕከላዊ ዞን በሚያዝያና ግንቦት ወራት በከፍተኛ ወጪ ሊከናወኑ ታስበው የነበሩ 2 ሺህ የሚጠጉ የሰርግና ሌሎች ድግሶች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደራዘሙ መደረጉን የክልሉ ግብረ ኃይል ገለፀ ።

ለድግስ ሊወጣ የነበረ 53 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር  ተቆጥቧል።

በዞኑ የኮሮና መከላከል ግብረ ሀይል  የጸጥታ ኮሚቴ ሴክሬታሪያት አቶ አብርሃ ተክሉ ለኢዜአ እንደገለጹት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ድንጋጌዎች  የሰዎችን መሰባሳብ ይከለክላሉ ።

ሰርግ፣ተዝካርና ሌሎች ድግሶችን ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት እንዳይሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌዎች  ገደብ ከተጣለባቸው መካከል ተጠቃሾች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በሚያዝያና ግንቦት ወራት ሊደረጉ ታስበው የነበሩ 1 ሺህ 976 የተለያዩ ማህበራዊ ድግሶች እንዲራዘሙና እንዲቋረጡ ተደርጓል ።

በተለይም የ800 ጥንዶች ሰርግ  በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለማካሄድ ባለመቻሉ ለሌላ ጊዜ እንዲረዘም መደረጉን አስረድተዋል።

292 የተዝካር ድግሶች እንዲራዘሙና ሌሎች  884  ማህበራዊ ድግሶች  እንዲቋረጡ መደረጉን ከአቶ አብርሃ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

በዞኑ ግብረ ሀይል የኢኮኖሚ ጉዳይ ንኡስ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ጽገ ተስፋይ በበኩላቸው ሁለት ሺህ ለሚጠጉ ልዩ ልዩ ማህበራዊ ድግሶች ወጪ ሊደረግ ታስቦ የነበረ ከ53ነጥብ3 ሚሊዮን ብር በላይ ማህበረሰቡ እንዲቆጥበው መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ሃብት ማባከን ተገቢ አይደለም ያሉት አስተባባሪው ማህበራዊ ድግሶች በመቅረታቸው እና ወጪውን በመቆጠቡ ኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በዓድዋ ከተማ ምዕባለ ከተማ ነዋሪ አቶ ፍጹም ነጋሲ በሰጡት አስተያየት ኮሮና ከመከሰቱ በፊት ሴት ልጃቸው ለመዳር  100 ሺህ ብር መድበው  ዝግጅት ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል የወጣውን ድንጋጌ በማክበር  ከእጮኛዋና ቤተሰቡ ጋር በመመካከር የሰርግ ፕሮግራሙ  ለቀጣይ አመት እንዲራዘም   መወሰናቸውን ተናግረዋል።

''መንግስትና ህዝብ ቫይረሱ ለመከላከል እየሰራ ነው ''ያሉት አቶ ፍጹም የጤና ጉዳይ መቅደም ስላለበት በሰርጉ መራዘም ምንም  እንዳልተከፉ ገልፀዋል ።

በአንጻሩ ከፍተኛ ወጪ ከማውጣት እንድንቆጥብ አድርጎናል ብለዋል ።

ሰርግ ለመደገስ የተያዘውን እቅድ በመሰረዝ ከእጮኛው ጋር በቤተክርስቲያን  ውስጥ ጋብቻቸውን እንዳከናወኑ የተናገረው ደግሞ በአክሱም ከተማ የሓየሎም ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በሪሁ አብርሃ ነው።

ወላጆቹ ቤተዘመድና ጎረቤት ለመጥራት ከፍተኛ ወጪ በማድረግ ለሰርግ ይዘጋጁ እንደነበር ጠቅሶ  በአዋጁ ምክንያት የሰርግ ድግስ በማስቀረት ያለምንም ወጪ ሀዝብ ሳይሰበስብ በቤተክርስትያን ስርአት ጋብቻው መፈጸሙ እንዳስደሰተው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም