በባህርዳር ከተማ 260 ባጃጆች ተይዘው ጉዳያቸው እየተጣራ ነው

ባህርዳር፣ ግንቦት 15/2012 በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በህገ ወጥ ተግባር ተሰማርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ 260 ባለ ሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ መጀመሩን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት መቆጣጠርና መከታተል መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሙሉጌታ በዜ ለኢዜአ እንደገለጹት ባጃጆቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ በተወሰደ እርምጃ ነው።

በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰማሩ ባጃጆች ኮድ 1 መሆን ሲገባቸው አሁን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉት ግን በኮድ 2 ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው ብለዋል ።

ኮድ 2 ሰሌዳ የሚያወጡ ባጃጆች ለቤት እንቅስቃሴ እንጂ በትራንስፖርት ዘርፍ የመሰማራት ፈቃድ የሌላቸው ቢሆንም በባህርዳር ከተማ ግን በኮድ 2 በርካታ ህገ ወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ እንደነበር ኮማንደሩ ተናግረዋል ።

በህገወጥ ንግድ ፣ ዝርፊያና ቅሚያን ጨምሮ አስነዋሪ ድርጊት በመፈፀም ህብረተሰቡን ለምሬት ሲዳርጉ የቆዩ ናቸው ብለዋል ።

ባጃጆቹ በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት አንዳንዶቹ በውስጣቸው ለህገ ወጥ ድርጊት መፈፀሚያ የሚውሉ ስለቶች ፣ ብረታብረት፣ ሰንሰለት፣ የጦር መሳሪያና ጥይት ተገኝቶባቸዋል ።

አስፈላጊውን ማጣራት በማካሔድ በተለያዩ ወንጀሎች ተሳታፊ የነበሩ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ ህግ የማቅረብ ተግባርም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም