ቀጥታ፡

የንግድ እና ግብይት አካባቢ ኮሮናን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ለመተግበር ጥረት እየተደረገ ነው

ባህርዳር፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የንግድ እና ግብይት አካባቢዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በመንግስት የወጣውን መመሪያ ለመተግበር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በነዚህ አካባቢዎች ቫይረሱን በመከላከሉ በኩል መዘናጋት እንዳይኖር በፌደራል ደረጃ  የወጣውን የንግድ ዘርፍ መመሪያ ቁጥር 3/2012 አስመልክቶ ቢሮው መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባልና የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ በዚሁ መግለጫቸው ቫይረሱን ለመከላከል  መጀመሪያ አካባቢ የነበረው የተጠናከረ ስራ አሁን ላይ በመዘናጋት  በቸልተኝነት እየታለፈ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በኮሮና ቫይረስ የተያዘው ሰው ቁጥር ዝቅተኛ አድርጎ መውሰድና በሀገር ደረጃ የሟቾች ቁጥር አነስተኛ  መሆን በሽታውን ገዳይ አድርጎ ያለመውሰድ ችግር በስፋት እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

ከንግድና ግብይት ስርዓቱ አለመስተካከል ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የኮሮና ቫይረስ መስፋፋትን ለመግታትም ቀደም ብሎ በወጣው አዋጅና ደንብ ያልተካተቱ ጉዳዮችን በፌደራል ደረጃ አዲስ መመሪያ መውጣቱን አስታውቀዋል።

መመሪያውም አምራች ፣አከፋፋይ ፣ቸርቻሪና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች  የንጽህና መጠበቂያ መገልገያዎች  በበራቸው ላይ በማስቀመጥ ደንበኛቸው ተጠቅመው  መገበያየት እንዳለባቸው ያስገድዳል።

ደንበኞችም እጃቸውን በሳሙና ሳይታጠቡም ሆነ ሳኒታይዘር ሳይተጠቀሙ አገልግሎት ማግኘት እንደማይችሉና  በሁለት ሜትር ርቀት በወረፋ መገበያየት ይጠበቅባቸዋል

የአገልግሎት ሰጪ ድርጅት ሰራተኞችም  የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲሁም ጓንት የማድረግ  ግዴታ በመመሪያው  ከመቀመጡም በላይ አስተናጋጅና ገንዘብ ተቀባይን በመለያየት ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩም እንዲሁ።

የህብረት ስራ ማህበራት በጥንቃቄ  ምርቶቻቸውን በመሸጫ ሱቆቻቸው እና በየአካባቢው በማዘዋወር ለሁሉም ተጠቃሚ ክፍሎች የማድረስ ግዴታ እንደተጣለባቸው ያመለከቱት አቶ ተዋቸው ደንበኞችም ባሉበት ሆነው የሚፈልጉትን ምርት አዘውትሮ ማስመጣት ይችላሉ ብለዋል።

መጠጥ ቤቶች ፣" ጂም "እና "ዲኤስቲቪ"  ቤቶች ያሉ በርካታ ሰው ተጠጋግቶ የሚቀመጡባቸው ቀድሞ በወጣው አዋጅ እንዲዘጉ መደረጉን አስታውሰው  በአዲሱ መመሪያም ተግባራዊ ሆነው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የከተማ እና  የወረዳ አስተዳደሮች  ደግሞ ተጨማሪ የገበያ ቦታዎችን በማዘጋጀትና በማስፋፋት የሚፈጠረውን መጨናነቅ  ለመቀነስ መስራት እንዳለባቸው በመመሪያው መደንገጉን አመላክተዋል።

አቶ ተዋቸው እንዳሉት በመመሪያው የተቀመጡ ግዴታዎችን በማይፈጽሙና በማያስፈጽሙ የንግድ ድርጅቶች ላይ ፈቃድ የመሰረዝ፣ ድርጅታቸውን የመዝጋትና ወደ ህግ በማቅረብ እስከ ማስቀጣት ኃላፊነት ለቢሮው ተሰጥቶታል።

መመሪያውን ለማስፈጸምም በቢሮው አስተባባሪነት የፍትህ አካላት፣ ጤና ቢሮና የአስተዳደር ጽህፈት ቤቶችን ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም