ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተቀዛቅዟል

ሐዋሳ፣ ግንቦት 14/2012  (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በግብዓት እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ወረርሽኙን ለመከላከል የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መቀዛቀዝ ስጋት መፍጠሩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ገለፀ ።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው  የተፈጠረውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅም በማደጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ያለምንም መሳቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲበረታቱ እስከታች ድረስ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተደራሽ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

በማህበሩ የደቡብ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተሾመ ታከለ እንዳሉት ማህበሩ በመንግስት ታምኖበት የበጎ ፈቃድ ስራዎችን ለማስተባበር ሃላፊነት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

 በተለይ የወረርሽኙን መከላከያ ሃሳቦች በመንደፍ፣ ሃብት በማሰባሰብና ተግባር ላይ ለማዋል በርካታ ስራዎች እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስከ አሁን ማህበሩ ባደረገው ጥረት ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በማሰባሰብ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ሥራ አጋዥ እንዲሆን በክልሉ ለሚገኙ መዋቅሮች ተደራሽ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቫይረሱ መከሰት በተሰማ ጊዜ የነበረው መደናገጥና ጥንቃቄ በበጎ ፈቃደኞች በኩልም ሆነ በህዝቡ ዘንድ እየተቀዛቀዘ መጥቷል ብለዋል።

 በየዕለቱ ከጤና ሚኒስቴር በኩል የሚወጡ መረጃዎች የቫይረሱ ተጠቂ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክቱ በመሆኑ ወረርሽኙ አሳሳቢ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞች ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጡና ራሳቸውን እንዳይከላከሉ እየገጠማቸው ያለው የግብአት አቅርቦት እጥረት ፈተና እየሆነ መምጣቱን አመልክተው አቅም ያላቸውና በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉና እንዲያበረታቱ ጠይቀዋል።

እስከ አሁን የተሰሩ ስራዎችና ድካሞች ከንቱ ሆነው እንዳይቀሩና ከወረርሽኙ ስጋት እንድንላቀቅ  ሁሉም  ዜጋ በቁርጠኝነት እንዲነሳሳ ጥሪ አቅርበዋል።

በሃዋሳ ከተማ ፒያሳ አካባቢ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የራሱን አሻራ ለማሳረፍ በበጎ ፈቃደኝነት ከተሰማሩ  ወጣቶች መካከል ሃብታሙ ተስፋዬ አንዱ ነው።

ወጣቱ እንደሚለው የበጎ ፈቃደኞች የበኩላቸውን እየተወጡ ቢሆንም በመጀመሪያ አካባቢ የነበረው ጥንቃቄና ትኩረት ከመቀነሱም በላይ ማህበረሰቡ እየሰጠ ያለው ምላሽ፣ድጋፍና ሞራል እየተቀዛቀዘ መጥቷል።

ከሌሎች ሃገራት እንደሚሰማው ከሆነ የአንዱ በቫይረሱ መጠቃት በሌላው ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን በመረዳት ብንተሳሰብ መልካም ነው ሲል መልዕክቱን አስተላልፈዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውጤቱ የመንፈስ እርካታ በመሆኑ ምንም ሳይከፈለን ህዝብ ለማስተባበር ብንሞክርም የሚስተዋለው ቸልተኝነት አስፈሪ ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ በሃዋሳ ከተማ የሃይቅ ዳር ቀበሌ በጎ ፈቃደኛ ወጣት ሜሮን መሸሻ ናት።

በጎ ፈቃደኞች አቅማቸውን፣ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሰውተው የሚሰጡት አገልግሎት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ወደ ታች ወርደው እየገጠማቸው ያለውን የግብአት እጥረት እንዲመለከቱና በሞራል ደረጃ እንዲደግፉቸው ጠይቃለች፡፡

በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ወጣቶች ባላቸው አቅም ሁሉ እያደረጉት ያለው ተጋድሎና መተዛዘን የሚደነቅ ነው ብለዋል ።

ይህ ሲሆን ደግሞ ወጣቶቹ ቅድሚያ ራሳቸውን እንዲከላከሉ መደረግ አለበት ያሉት አቶ ርስቱ ሳይታሰብ የመጣ ዱብዳ በመሆኑ ግብአቶችን ገዝቶ ለማቅረብ በገበያው ላይ የምርት አቅርቦት ችግር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ 

የተለያዩ የሙያ ተቋማትና ግለሰቦች ባደረጉት  ርብርብ ችግሩን እየተሻገርን በመሆኑ በተለይ ጫናውንና ድካምን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎች እየተመረቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡          

በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት የሚያስችል አቅም በማደጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ያለምንም መሳቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡና እንዲበረታቱ እስከታች ድረስ አስፈላጊ ቁሳቁሶች ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል፡፡          

አሁን ላይ በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ርብርብ  ከ361 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኛች እየተሳተፉ እንዳሉ ከቅርንጫፉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም