በጋምቤላ የለይቶ ማቆያ እና የህክምና ማዕከል የግብአት ክፍተት መኖሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ የለይቶ ማቆያ እና የህክምና ማዕከል የግብአት ክፍተት መኖሩ ተገለጸ
ጋምቤላ፣ ግንቦት 14/2012 ( ኢዜአ) በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው የለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከል የግብአት ክፍተት መኖሩ ተገለጸ።
የክልሉ መንግስት ካቢኔ የዩኒቨርሲቲውን የለይቶ ማቆያና የህክምን ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጀሉ እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ መግባቱ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የመከላከሉ ስራ እየተከናወነ ይገኛል።
በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የተዘጋጀው ማቆያና የህክምና ማዕከል በሰው ኃይል በኩል በተሻለ መልኩ ቢደራጅም በህክምና ግብዓት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን በምልከታቸው ማረጋገጥ እንደቻሉ ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የሚታዩ ክፍተቶችን ደረጃ በደረጃ በመፍታት ወርርሽኙን ለመከላከል የጀመረውን ስራ አጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተለይም በክልሉ የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላብራቶሪ አለመኖሮ በሽታውን በመከላከሉ ስራ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት ግምት ውስጥ በማስገባት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመነጋገር አገልግሎቱን በቅርቡ ለማስጀምር ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪና የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በበኩላቸው ቫይረሱን ለመከላከል እንደ ትልቅ ፈተና ሆኑ የቆየውን የምርመራ ላብራቶሪ ችግር ለማቃለል የማዕከል ማደራጀትና ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ ስራ ሲጀምርም በቫይረሱ የሚገመቱ ሰዎችን ናሙና ወደ አዲስ አበባ ይላክ የነበረውን በማስቀረት በቅርበት የተፋጠነ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።
የለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎት ማዕከላትን የሚታዩ የግብዓት ችግር ለማቃለል ቢሮው ከጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በጋምቤላ ከተማ የሚገኘው የዩኒቨርሲቲው የለይቶ ማቆያና ህክምና ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ፍሬህይወት ጌታቸው ማዕከሉ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ማዕከሉ የተሟላ አግልግሎት ለመስጠት አሁንም የተወሰኑ የህክምና መሳሪያዎች እንደሚጎድሉት ጠቁመው ያልተሟሉትን የህክምና ግብዓቶች ለማሟላትም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ገልጸዋል።