ማህበሩ ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በለገጣፎ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ የተደረገው ከተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢ ተፈናቅለው በለገጣፎ ለሚገኙ 512 አባወራዎች ነው።
የሠራተኛ ማህበሩ ከ500 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ምግቦችንና የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ ቁሶችን ነው በዛሬው ዕለት ድጋፍ ያደረገው።
ድጋፉን የለገጣፎ-ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃቢባ ሲራጂ ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ተሊላ ደሬሳ በድጋፍ ርክክቡ ወቀት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉ ዜጎች በመድረስ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣት ሲሉ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
"ይህን የችግር ወቅት ማለፍ የምንችለው እርስ በእርስ በመረዳዳት ነው" ሲሉም ኢንጂነር ተሊላ ገልጸዋል።
ማህበሩ ከዚህ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ኮቪዲ-19ን ለመከላከል ለተቋቋመው ግብረ ሃይል የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም የማህበሩ ፕሬዚዳንት አስታውሰዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃቢባ ሲራጂ የኢትዮጵያ አየርመንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኞች ማህበር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ "መአድ እንጋራ" ጥሪን ተቀብሎ ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
"ማህበሩ በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ተገኝቶ ድጋፍ በማድረግ ከፌዴራል ተቋማት የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።
በምስራቅ ጎጃም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 250 አባወራዎችም በነገው ዕለት ድጋፍ እንደሚያደርግ ማህበሩ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር በ1955 ዓ.ም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች የተቋቋመ ማህበር ነው።