በባሌ ጎባ በባንክ ዝርፍያ የተከሰሰ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ጎባ በባንክ ዝርፍያ የተከሰሰ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ
ጎባ፣ግንቦት13/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሌ ጎባ ቅርንጫፍን ሰብሮ በመግባት የዝርፍያ ወንጀል የፈጸመውን ግለሰብ በአምስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ መደረጉን የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለፀ።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ሙክታር ሁሴን በተባለው ተከሳሽ ላይ ውሳኔውን ያሳለፈው ግንቦት 13 ቀን 2012 ዓ.ም በዋለው ችሎት ነው፡፡
ግለሰቡ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በጎባ ከተማ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሌ ጎባ ቅርንጫፍ አጥር በመዝለል ከገባ በኋላ መስኮቱን በብረት በመቆራረጥ ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቷል።
የገንዘብ ማስቀመጫ ካዝና የሚገኝበትን ክፍል በር ከሰበረ በኋላ ስራ ላይ የነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች ለጎባ ከተማ ፖሊስ አባላት በሰጡት ጥቆማ መሰረት እጅ ከፍንጅ ተይዟል።
ፖሊስና አቃቤ ህግ እጅ ከፍንጅ በተያዘው ግለሰብ ላይ የክስ መዝገቡን በማጣራት ለባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቅርበው እንዲከሰስ አድርገዋል፡፡
ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ድርጊቱን መፈጸሙን አምኗል፡፡
ክሱን የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ግለሰቡንና ሌሎችንም ያስተምራል በማለት በአምስት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጥቀስ መረጃውን ለኢዜአ ያቀበሉት የጎባ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ከዲር በከሬ ናቸው።